+251-993-818276 akofeda@gmail.com Addis Ababa, Ethiopia

ሆሣዕና

በዲን. በረከት አዝመራ

“እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ ዘንድ እንድትሆን እኔም በእነርሱ…።” (ዮሐ. 17፥26)
***
የሆሣዕና ባህል ለፋሲካ መሥዋዕት ወደ ኢየሩሳሌም የሚገቡ በጎች የአምሳልነታቸው ፍጻሜ የሆነው መድኃኒት ክርስቶስ “ኢየሩሳሌም የቀዳችለትን የመከራ ጽዋ ይጠጣ ዘንድ” ወደርሷ የገባበት ቀን መታሰቢያ ነው። በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘው የሕዝቡ ምስጋናም ድንቅ ነው! “ሆሳዕና በዓርያም፤ መድኃኒታችን ከላይ ከአርያም ነው፤ ይሁንልን” ብለው ዘምረዋልና። (ማቴ. 21፥9)
የመሥዋዕት ምሥጢር ምንድር ነው? መሥዋዕት ራስን በመስጠት የሚገለጥ እና ሞትን የሚያልፍ ፍቅር መገለጫ ነው። መሥዋዕት አንዱ ስለሌላው መሞት ነው! አንድ ሊቅ እንዳሉት መሥዋዕት “በጽኑ እና አሰቃቂ መከራ ውስጥ የሚገለጥ ፍቅር (tragic love)” ነው። ፍቅር ሲለየው መሥዋዕት ሞኝነት ይሆናል! አንዱ በሠራው ሌላው ለምን ይሞታል? ሞቱስ ፍቅር ከሌለ ፍትህ ሊኖረው እንዴት ይችላል? ፍትህ ግን ፍቅርን ይቀበላል!
***
ጌታችን ስለ እኛ ሊሠዋ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሰማያዊቷ የእግዚአብሔር መንግሥት በትህትና ተገልጣለች። በዚህም ምክንያት ፍቅሩን በአህያ ላይ በመቀመጥ ከጌትነቱ እና ከመንግሥቱ ጋር ገልጧታል። ሕዝቡም “የአባታችን የዳዊት መንግሥት ቡሩክ ነች” በማለት ለመንግሥቱ ምሥጋና አቅርበዋል። (ማር. 11፥10)
የእግዚአብሔር ፍቅሩ እና መንግሥቱ አንድ ነው። እግዚአብሔር ከአለም በፊት በመንግሥቱ እንደነበረ እንዲሁም በፍቅሩም ነበር። በፍቅር ውስጥ በሌላው ክብር መደሰት እና በግዴታ እና በተዋረድ (subordination) ሳይሆን በፈቃድ መገዛት አለና። በፍጥረት የማትገደበው የእግዚአብሔር መንግሥትም እንዲሁ በፍቅር ጸንታ ለዘላለም ነበረች፤ ትኖራለችም።
በወንጌል “እግዚብሔር ፍቅር ነው” ተብለን ተምረናል። ለዓለም ሃይማኖተኞች ሁሉ አንድ ጥያቄ እንጠይቅ። ዓለም ሳይፈጠር (እግዚአብሔር ይወደው ዘንድ ከርሱ ሌላ አካል ሳይኖር) የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት ይገለጥ ነበር? የእግዚአብሔር ፍቅር በፍጥረታት መኖር ላይ ተወስኖ የሚሠራ (conditional) ነበር ማለት ነውን? ፍጥረታት ሳይኖሩ ፍቅሩ የሚሠራ ሳይሆን ወደፊት ፍጥረታት ሲኖሩ የሚሠራ (potential) ነበር ማለት ነውን? ወይስ አንድ አካል አንድነቱን ከሁለት ሳይከፍል እና ጽኑ አንድነቱን (simplicity) ሳያጣ እውነተኛውን መሥዋዕታዊ ፍቅር በራሱ ላይ ሊያሠራ ይችላልን? እግዚአብሔር ከዓለም በፊት ፍቅሩ እና መንግሥቱ እንዴት ይገለጥ እና ይሠራ ነበር? እግዚአብሔር አንድ አካል ነው የሚሉ መልሳቸውን ለራሳቸው ይመልሱ፤ ከቻሉ ለእኛም ይንገሩን።
***
ይህ ዘላለማዊ የፍቅር ምሥጢር በምሥጢረ ሥላሴ ለምናምን ለእኛ ለክርስቲያኖች የተገለጠ ነው።
ፍቅር በሦስት አካላት ይጸናል። የሚወድድ እና የሚወደድ ሁለት አካላት ካሉ አይበቃምን? ለፍቅር ሦስትነት ለምን ያስፈልጋል? የሚል ይኖራል። አይበቃም! በወዳጁ እና በተወዳጁ መካከል ሆኖ ያለ ቅንዓት በፍጹም ደስታ የሚቆም (በዚህም በወዳጁም በተወዳጁም በመወደድ የፍቅሩ አካል የሚሆን) ሦስተኛ አካል ሲኖር ፍቅር ፍጹም ይሆናል። የመረዳት አቅማችን ጥቂት ቢሆንም ይህ ጥልቅ ፍቅር በቅድስት ሥላሴ አካላት ውስጥ ለዘላለም እንዳለ እና እኛን የወደደባት ፍቅሩም ከዚህች መለኮታዊ ፍቅሩ ጋር አንድ እንደሆነች ጌታችን “እኔን የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን” በማለት ገልጦልናል። (ዮሐ. 17፥26) በእውነቱ ለዚህ ፍቅር የተጠራን ሁሉ ምንኛ የታደልን ነን!
***
በዚህ ሰሙነ ሕማማት በምናስበው የክርስቶስ መከራ እና ሞት የተገለጠው ፍቅር በሦስትነት ያለ የአንዱ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው! በምዕራቡ ዓለም ክርስትና (በአንዳንድ የፕሮቴስታንት ስብስቦች) ፍቅርን ለወልድ ቁጣን፣ መዓትንና ርግማንን ደግሞ ለአብ የመስጠት ባህል አለ። ወልድ ከአብ ያዳነን ያስመስሉታል። ያዳነን ፍቅር ግን ለዘላለም በቅድስት ሥላሴ ያለው የእግዚአብሔር አንድ ፍቅር ነው። ፍርዱ እና ርግማኑም እንዲሁ በአንዱ በእግዚአብሔር ያለ ነው። ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍቅርን እና ፍርድን በአካላት መካከል አትለያይም። በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን እና ሞት የተገለጠው ፍቅር የአብ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ ዘላለማዊ ፍቅር ነው። ጌታችን እንዳስተማረን “እርሱን በወደደበት ፍቅሩ የወደደን” አብ ነው። በመሞት የወደደን እርሱ ወልድ ነው። ከሐጢኃት ሲያነጻን ሲቀድሰን የሚኖር መንፈስ ቅዱስም በዚሁ አንድ ፍቅር የሚወደን እርሱ ነው።
***
መልካም ሰሙነ ሕማማት ይሁንልን!

Please follow and like us:
error0
fb-share-icon20

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Post

ሠማያት ተከፈቱ

ውድ ወንድሞች፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በጽርሐ-ጽዮን በላይኛው ቤት ስለ ተሰራጨው መንፈስ ቅዱስ የበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለትን አስመልክቶ ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ እነዚህ ተካተዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ከሰማይ መና ወይም እሳት ሳይሆን የወረደው የመልካም ነገሮች

ሞትን በሞት የሻረ

በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊምንጭ፡ The Fathers of the Church Patristic Series 91 ጌታችን በሞት ላይ ተረማመደ፡፡ ከሞት ባሻገር ላለ መንገድም መረማመጃን አዘጋጀ፡፡ በሞት መንገድ ሞትን ያለፈቃዱ ያስወግደው ዘንድ በፈቃዱ ለሞት የተገዛ

ማነው እንደ መጻጉዕ ያልታመመ?

ጸሎት እንዴት ተወዳጅ ነገር ነው፡፡ ሥራውስ እንዴት ያማረ ነው፡፡ ጸሎት ከመልካም ሥራ ጋር ሲደረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ በይቅርታ መንፈስም ሲደረግ፤ ወደ ላይ ሲያርግ ሁሉ ይታወቃል፡፡ ከልብ የተደረገ ንጹህ ጸሎት