+251-993-818276 akofeda@gmail.com Addis Ababa, Ethiopia

ማነው እንደ መጻጉዕ ያልታመመ?

ጸሎት እንዴት ተወዳጅ ነገር ነው፡፡ ሥራውስ እንዴት ያማረ ነው፡፡
ጸሎት ከመልካም ሥራ ጋር ሲደረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡
በይቅርታ መንፈስም ሲደረግ፤ ወደ ላይ ሲያርግ ሁሉ ይታወቃል፡፡
ከልብ የተደረገ ንጹህ ጸሎት ሁል ጊዜ መልስ አለው፡፡
ጸሎት በእግዚአብሔር ፀጋ ሲሞላ ርቱዕ
ነው፡፡
የፋርሱ አፍረሃት

The Book of Mystical Chapters by John MCGUCKIN

ይህ የአቢይ ጾም 4ኛ ሳምንት በቅድስት ቤተክርስቲያናችን መጻጉዕ ተብሎ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሳምንት ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያየ ደዌ ሥጋ የተያዙ ህሙማንን መፈወሱን፣ የዕውራንን ዓይን ማብራቱን ባጠቃለይ በብዙ ደዌ ሥጋ የተያዙ ሰዎችን መፈወሱን የምናስብበትና እና ከደዌ ነፍስም ድኅነት የሚገኝበት መድሐኒት እርሱ መሆኑ የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡

ጌታ ለጌትነቱ ምስክርነት ያደርገው የነበረው ድውያንን የመፈወስ ዜና ከኢየሩሳሌም ውጭ ባሉ ሀገራት በሁሉም አቅጣጫ በመሰማቱ ሰዎች ከየቦታው ወደ እርሱ ይመጡ እንደነበር ወንጌል ይነግረናል፡፡ በዚህ መልኩ ወደ እርሱ የመጡትን ለምጻሞች፣ ንዳድ ያለባቸውን፣ ዕውራንን፣ ጎባጦችን፣ አንካሶችን፣ እጃቸው የሰለለባቸውን፣ አጋንንት ያደረባቸውን በመፈወስ እና ሙታንን በማስነሳት ጌትነቱን አስመስክሯል፡፡ ጌታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት በላይ ብዙ ድውያንን የፈወሰ ቢሆንም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 23 ድውያን እና 3 ሙታን ብቻ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡

ከዛ በበለጠ የጌታችንም ሆነ የቅድስት ቤተክርስቲያን ዋና ጭንቀት የሰው ልጆች ነፍስ ድኅነት ነው፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ ነፍስ ማደሪያ ተብላ የምትጠራው ልቦና (Nous) ባለመንጻቷ እና በክፉ ደዌ በመያዟ ምክንያት የሰው ልጅ ለመዳን የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንዳያገኝ እና የዛሬው መጻጉዕ ተብሎ እንዲጠራ ምክንያት ሆናለች፡፡

የልቦና ዋናው ሥራ አዘውትሮ ፈጣሪን ማሰብ ብቻ ሲሆን ሌሎች መልካም ነገሮች ሁሉ ተጓዳኝ ሥራዎቹ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁን ሰዓት የሰውል ልጅ ልቦና፤ ዋናው ሥራው የሆነውን ፈጣሪን ማሰብ  አይደለም መልካም ነገርን እንኳን ማድረግ ተስኖት ዕለት ዕለት ክፋትን በማሰብ እና ክፋትን በማድረግ ተጠምዷል፡፡ በዓለማችን የምናየው ጭንቀት እና መከራም የዚህ ትሩፋት ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔርን ለማየት ወደሚያደርሰው ንጽሐ ልቦና ለመድረስ የሰው ልጅ ከሁሉ አሰቀድሞ ከክፋት መራቅና መልካም ነገርን ማድረግ መጀመር አለበት፡፡ ይህም የሚጀምረው በርቱዓ ሃይማኖት የመጻጉዕ ምዕራፍ ክፍል ላይ እንደተገለጸው ከመስጠት/ከመመጽወት/ ነው፡፡  ምጽዋትም ከጾም የሚገኝ በረከት ነው፡፡

ስጦታ /ምጽዋት/ ገጽን ሳያዩ ፣በሃይማኖት፣ በሀገር ልጅ(በብሔር)፣ በብልጽግና (ብድር ይመልስልኛል በሚል)፣  ሳያዳሉ፣ በተለይም አብዝተው የተቸገሩትን በማሰብ መደረግ ያለበት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስም የቤተክርስቲያን ትውፊትም ይነግረናል፡፡ በተለይ ስለ ሃይማኖታቸው ብለው በገዳም፣ በፍርኩታው፣ በምድር ጉድጓድ ውስጥ ለሚገኙት እና አብዝተው ለተቸገሩት አብዝቶ ቸርነት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ የሃይማኖት ሰዎች፣ የሚመጣው ዓለም ገዢ ስለሆኑ ለነዚህ ጻድቃን ውለታ ማስቀመጥ በኋላ ከሚያገኙት እርስታቸው ተካፋይ ሊያደርገን ስለሚያስችል በደስታ ልናከናውነው ይገባናል፡፡

ከዛም ባሻገር ዛሬ በዓለማችን ብሎም በሀገራችን የተከሰተውን የበሽታ ወረርሽኝ (የኮሮና ቫይረስን) ዜና ምክንያት በማድረግ በዜጎች ላይ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት እና ዜጎች በሚበሉት፣ በሚጠጡት እንዲሁም ጤናቸውን ለመጠበቅ በሚረዳቸው ሸቀጥ ላይ ከፍተኛ ዋጋ በመጨመር እነሱን ማስጨነቅ እግዚአብሔርን የሚያሳዝነው ሲሆን በተለይ የዐቢይ ጾምን በመጾም ከመጾም እና ከመጸለይ የሚገኘውን ትሩፋት ተስፋ የምናደርግ ክርስቲያን ነጋዴዎች ይህን ያልተገባ ነገር ማድረግ ከበረከት ይልቅ መርገምን የሚያመጣብን ስለሆነ አገልግሎታችን ይባረከልን ዘንድ፤ እግዚአብሔር የሚሰጠን ይበቃናል በማለት ማኅበረ ምዕመናንን ልናረጋጋ እና ልናዝንላቸው ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ ምንም የሌላቸውን እና የተቸገሩትን ልንረዳቸው /ልንመጸወታቸው/ ይገባል::

ይህቺ የጾም ፍሬ የሆነች ስጦታም በመልካም ንግግር (በመስጠታችን ሳንታበይ፣ ሳንቆጣ)  እና በእንባ በተደገፈ ጸሎት የታገዘች መሆን አለባት፡፡ ቅዱሳን አባቶች ከስጋ ደዌ ባሻገር ነፍሳችንም  ከተያዘችበት ክፉ ደዌ ትድን ዘንድ ህክምና ያስፈልጋታል ይላሉ፡፡ ይህም ልቦናችንን አስጨንቆ ከያዘው ክፉ ሃሳብ ማላቀቅና፣ ነጻ ማውጣት ይገባል ሲሉን ነው፡፡ ልመና፣ ምልጃ፣ ጸሎት፣ ልቅሶ፣ ሰቆቃ፣ መጨነቅ እነዚህ ሁሉ ኃጢአትን ከማስታወስ የሚወለዱ ናቸው፡፡

ስለዚህ የነፍስ ድኅነት የሚገኘው ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን በማሰብ ጸሎት ስናደርግ ነው፡፡ በእንባ የተደገፈ ጸሎትም ለኃጢአታችን የምናቀርበው መስዋዕት ነው፡፡ ጸሎትንም እንዳናስታጉል ጸሎት እንድናደርግ የተመደቡ ሰዓታት የታወቁ በመሆናቸው በእነዚህ ሰዓታት ጸሎት ማድረስ ይኖርብናል፡፡ ከዛ ልቦናችንን ሳያቋርጥ እግዚአብሔርን ወደሚያስብብት እና ሳያቋርጥ ወደሚጸልይበት ደረጃ እናደርሰዋለን፡፡ ጌታም የወደድነውን ይሰጠን ዘንድ በምንጸልይበት ጊዜ እጃችንን በመዘርጋት፣ በአንቃእዶ ልቡና የጸሎታችንን ውጤት እስከምናገኝ ድረስ በምልጃ ሳናቋርጥ መጨቅጨቅ ይገባናል፡፡

አብዝቶ ሳያቋርጥ የሚጸለይበት ደረጃ የደረሰ ሰው ልቦናውን ከክፉ ሐሳብ እንዲሁም ከመልካም ሐሳብ ጭምር ባሻገር ወዳለው ከፍታ ወደ እግዚአብሔር ከፍ በማድረግ የመንፈሳዊ ሕይወት ከፍተኛ ደረጃ ወደ ሆነው ወደ ንጽሐ ልቦና ይሸጋገራል ማለት ነው፡፡ እዚህ ከፍታ ላይ የደረሰ ሰውም ከሌሎች መሰሎቹ ጋር ያለ ንግግር በልቦናው ብቻ መግባባት ይችላል፡፡ ይህም ማለት በመንፈስ መነጋገር ማለት ነው፡፡ የዚህ ጸጋ ባለቤቶች አጠገባቸው ካለ ሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ይህ ጸጋ ከተቸራቸው በቦታ ከእነሱ ጋር ከሌሉ እና በዓለም ላይ በማንኛውም ጥግ ካሉ መሰሎቻቸው ጋር በመንፈስ ይነጋገራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የተሰወረውን የሰው ኃጢአት እና ክፉ ሐሳብን ጭምር መግለጥ ሲችሉ፤ በተሰጣቸው ሀብተ ትንቢትም (ወደፊት የሚሆነውን ማወቅ) መጻዒውን ነገር መናገር ይችላሉ፡፡

እነደነዚህ አይነት አባቶች በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ውስጥ ያሉና የሞሉ ሲሆን፣ እኛ ለንሰሃ ወደ እነሱ ስንቀርብ አፋችንን መክፈት ሳንጀምር በፊት  የተሸሸገ ክፉ ሐሳባችንን፣ ለማንም ያልገለጽነውን ክፉ ድርጊቶቻችንን /ኃጢአታችንን/  እንዲሁም በዚህ ክፋታችን የምንቀጥል ከሆነ ሊደርስብን የሚችለውን አደጋ ይነግሩናል፣ ይመክሩናል፣ የነፍስና የሥጋ መድኃኒት ከሆነው ከክርስቶስ ሥጋ እና ደም እንድንደርስ ያግዙናል፡፡

በመሆኑም የሰው ልጅ ከሥጋ ደዌ ጤነኛ ቢሆን ከነፍስ ደዌ ማለትም ከልቦና ሕመም (ክፉ ከሚያስብ ልብ፣ ለዚህ ዓለም ኑሮ ብቻ ከሚጨነቅ ልብ፣ እግዚአብሔርን ከሚዘነጋ ልብ) ነጻ ስላልሆን የጌታችንን መድኃኒትነት ተስፋ በማድረግ፤ እንድንበት ዘንድ የሰጠንን እና ቅዱሳን አበው ‹‹የሞት መድሐኒት ብለው የሚጠሩትን›› ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን ለመብላት እና ለመጠጣት እንችል ዘንድ ልቦናችንን በማንጻት እንቅረብ፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል

Please follow and like us:
error0
fb-share-icon20

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Post

ሞትን በሞት የሻረ

በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊምንጭ፡ The Fathers of the Church Patristic Series 91 ጌታችን በሞት ላይ ተረማመደ፡፡ ከሞት ባሻገር ላለ መንገድም መረማመጃን አዘጋጀ፡፡ በሞት መንገድ ሞትን ያለፈቃዱ ያስወግደው ዘንድ በፈቃዱ ለሞት የተገዛ

የዐቢይ ጾም ቃለ ምዕዳን በብፁዕ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ባስሊዮስ

ብፁዕ አባታችን በነበሩበት ወቅት ለኢትዮጵያ ሀገራችን እና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ብዙ አስተዋጽኦዎችን ያደረጉ ሲሆን በተለይ በሚመለከተቻው የመንፈሳዊ አገልግሎት ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ከማሳነጽ ጀምሮ በተለያዩ አድባራትና ገዳማት በመዞር አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎችን አድርገዋል፡፡

ኦርቶዶክሳዊ አባት ፍለጋ

‹‹ቤተክርስቲያን ያለ ጠባቂ ነበረች መልካም የሆነ ጠፍቶ ክፋት ግን በሁሉ ቦታ ነበር ፡ወቅቱ መብራት በሌለበት ጭለማ እንደመጓዝ ነበር፡፡ ክርስቶስ ተኝቶ የቁስጥንጥንያ ባሕር ለተወሰነ ጊዜ በአርዮሳውያን እጅ ነበር፡፡ በዚህ ያገኘሁት ምንም