+251-993-818276 akofeda@gmail.com Addis Ababa, Ethiopia

የዐቢይ ጾም ቃለ ምዕዳን በብፁዕ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ባስሊዮስ

ብፁዕ አባታችን በነበሩበት ወቅት ለኢትዮጵያ ሀገራችን እና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ብዙ አስተዋጽኦዎችን ያደረጉ ሲሆን በተለይ በሚመለከተቻው የመንፈሳዊ አገልግሎት ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ከማሳነጽ ጀምሮ በተለያዩ አድባራትና ገዳማት በመዞር አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎችን አድርገዋል፡፡ ብፁዕ አባታችን የቅድስት ቤተክርስቲያንን ዓመታዊ በዓላት በማስመልከት ብዙ ቃለ ምዕዳን ለምዕመናኑ በማስተላለፍ የሚታወቁ ሲሆን እኛም ዛሬ በዘመናቸው ዐቢይ ጾምን አስመልክተው ካስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ውስጥ በ1946 በየካቲት 26 ያስተላለፉትን ጣፋጭ ትምህርት እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡ በረከታቸው ይደርብን፡፡

አስተብቁዐክሙ አኀዊነ በሣህሉ ለእግዚአብሔር ትረስዩ ነፍሳትክሙ መስዋዕተ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ወሕያወ ወሥሙረ ወኅሩየ ይኩን ቁርባንክሙ ወቅኔክሙ ነባቢ ኢታፍቅርዎ ለዝዓለም ወሐድሱ ልብክሙ ወአመክሩ ዘይፈቅድ እግዚአብሔር ዘሠናይ ወዘጽድቅ ወዘፍጹም፡፡ ሮሜ 12፡ -3

ሐዋርያው ሰውነታችንን የእግዚአብሔር ማገልገያ አድርገን በመንፈሳዊ ሥራ መንፈሳዊ ክብርን እንድናገኝና እንድንጠቀም እንዲህ እያለ ይማልደናል፡፡

ወንድሞቻችን ሆይ ሕያው ለሚሆን ለእግዚአብሔር ሰውነታችሁን የከበረ መሥዋዕት አድርጉ ብዬ በእግዚአብሔር ይቅርታ እማልዳችኋለሁ፡፡ ቁርባናችሁ የተወደደ የተመረጠ ይሁን፡፡ መገዛታችሁም በዕውቀት ይሁን፡፡ ይህን ዓለም አትውደዱት ዕውቀታችሁን አድሱ፣ እግዚአብሔር የሚወደውን መርምሩ፣ የበጎውን፣ የእውነቱን፣ የፍጹሙን ያዙ፡፡

የእግዚአብሔር ጸጋ በተዋሐደው ቃሉ እንዲህ እያለ በጾም፣ በጸሎት፣ በሰጊድ፣ በአስተብርኮትና በልዩ ልዩ ፈተና (ጸዋትወ መከራ) ሰውነታችንን ቅዱስ መሥዋዕት አድርገን ወደ እግዚአብሐር እንድናቀርበው መማለዱ ከዚህ ዓለም ተድላ ርቀን ለመንግሥተ ሰማያት ክብር የተገባን ሆነን እንድንገኝ ነው፡፡

ሥጋችንን ለማስመቸት የምናደርገው የዚህ ዓለም ተድላ ደስታስ ይቅርና ነፍሳችንን ለማስመቸት የምንቀበለው የዚህ ዓለም ፈተና በወዲያኛው ዓለም የምናገኘውን የመንግሥተ ሰማያትን ክብር ሊመጣጠነውና ሊተካከለው አይችልም፡፡ ሮሜ 8፡18-22

ስለዚህ ሰውነታችን ክቡር መሥዋዕት ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚችለው ከዚህ ዓለም ተድላ ለይተን ዋጋ በሚያሰጡን ልዩ ልዩ ፈተናዎች ላይ ስንጥለው ነውና የተቀበልነው ማናቸውም (መከራ) ከመንግሥተ ሰማያት ክብር ጋር የማይመጣጠንና የማይወዳደር መሆኑን መገንዘብ፣ ከጾም ከጸሎት፣ ከሰጊድ፣ ከቀዊም የተነሣ የሚመጣውን ድካም እየታገሥን እንዲራራልንና የመንፈሳዊ ሥራችንን ጉድለት በቸርነቱ እንዲመላልን በተስፋ ጸንተን እናመልክት፡፡

በደግነቱና በትሩፋቱ የታወቀው ሊቁ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ዮሐንስ አፈወርቅም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በአባትነቱ ሲማልደን እንዲህ ብሏል፡፡

አስተብቁአክሙ ኦ ፍቁራን ከመ ትረስይዎ ለሥጋ ጽኑዐ ወአኮ ድኩመ፤ ሥጋችሁ በተድላ እንዲደክም ሳታደርጉ በመከራ እንዲጸና ታደርጉት ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡ ወአኮ ዘእቤ ዘንተ በእንተ ዕደው ባሕቲቶሙ አላ ለአንስትኒ፤ ይህንን የተናገርኩ ለሴቶቹም ነው እንጂ ለወንዶች ብቻ አይደለም፡፡ ተግሳጽ 29

ሊቁ የተነሳው ለመንፈሳዊ ሥራ አጋዥ ሆኖ ነውና ሥጋችሁን በመከራ እንዲጸና አድርጉት ያለን እንዲጾም፣ እንዲጸልይ፣ እንዲሰግድ ከእነዚህም ከፍ ያሉትን ጸዋትወ መከራ እንዲቀበል በትዕግስት አበርቱት ሲል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ዛቲ ጾም ኃዘን ለአብዳን ወፍሥሓ ለጠቢባን በማለት የጾምን ሥርዓት አክብሮ ተናግሯል፡፡ የሁሉ መሪ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሥጋችንን በተድላ በደስታ ሳናደክም የነፍሳችንን ሥራ እንድንሠራበት ሲያዝዘን፤ ዘይረክባ ለነፍሱ ይግድፋ ወዘሰ ገደፋ ለነፍሱ በእንቲአየ ይረክባ፡፡   ነፍሱን የሚያገኛት ሁሉ ያጠፋታል፣ ነፍሱንም ስለ እኔ ያጠፋት ያገኛታል ብሎዋል፡፡ ማቴ 10፡39

ብፁዓን ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት ይህንኑ የመሪያቸውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በመከተል ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራን በመቀበል ከሥጋዊ ምቾት ተለይተው የነፍስ ዋጋ የሚገኝበትን ሥራ እየሠሩ የዘለዓለም ሕይወት፣ ጣዕም፣ ተድላ፣ መዓዛ፣ ብርሃን ላለበት መንግሥተ ሰማያት የበቁ ሆነዋል፡፡

ሐዋርያት ሰማዕታት የዐላውያንን እሳትና ስለት ጻድቃን (ባሕታውያን) ዕፀበ ገዳምን፣ ግርማ ሌሊትን፣ ድምፀ አራዊትን ታግሠው ከፍ ከፍ ያለ መከራ ለተቀበሉላት መንግሥተ ሰማያት እኛ በጾም በጸሎት በሰጊድ በቀዊም ሰውነታችንን ወስነን ገተን ብንይዝላት ይበዛብናል? ወይስ ጾም ጸሎትና መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ ለክርስቲያን የተገባ መሆኑን የሚዘነጋ አለን?

አንዳንድ ሰዎች በወጣትነታችን ዘመን መጾም፣ መጸለይ፣ መስገድ፣ መቁረብ አይቻለንም እያሉ ይሳሳቱ ይሆናል፡፡ እንዲህ ማለት ለክርስቲያን የሚገባ አይደለም፡፡

ንጉሥ ሰሎሞን በሕጻንነትና በወጣትነት ወራት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ ሥራን መሥራት እንዲገባ ሲናገር፤ ተዘከሮ ለፈጣሪከ በመዋዕለ ውርዙትከ ዘእንበለ ይምጻእ መዋዕለ እኩይ ወይብጽሓ ዓመታት በዕለተ ትብል ኢኮነኒ ቦቶን ፈቃድየ፤ በሕፃንነትህ ወራት ፈጣሪህን አስብ የጭንቀት ቀን ሳይመጣ ደስ አያሰኙኝም የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ ብሏል፡፡ መክ 12፡1

በሕፃንነት ወራት ጀምሮ እግዚአብሔርን ማሰብና መንፈሳዊ ሥራን መከታተል እንዲገባ እንዲህ የተባለ ሲሆን ዐርባ ዓመት አምሳ ዓመት ካልሞላኝ ዓቢይ ጾምን አልጾምም አፌን በጸሎት ጉልበቴን በስግደት፣ ሕሊናዬን በትጋህ ሌሊት አላደክምም እያሉ የቡዋልት የሥላቅ ነገር መናገር ከክርስቲያን ሥርዓት መውጣት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቆሮንቶስ በረሃ ገብቶ ዐርባ ቀን ዐርባ ሌሊት ሙሉ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ መጾሙ ቅዱስ አርአያውን ለኛ ለመስጠት ስለኾነ በሕፃንነቴ ወራት ጌታ እንደጾመ አልጾምም ማለት ሕፃንነቴን ወይም ወጣትነቴን ለእግዚአብሔር አላስገዛም ማለት መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡

ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅም ጾም፣ ጸሎት፣ ሰጊድ፣ ቁመት በበለጠ ሊሠራ የሚቻለው ኃይለ ሥጋ በሚበረታበት በወጣትነት ዘመን መሆኑን ሲያስረዳ በሕፃንነት ወራት የተጀመረውን የትሩፋት ሥራ በእርጅና ጊዜ መተው አይገባም ብሎ ከተናገረ በኋላ፤ ለእመኮነ ምግባረ ሥጋ ይደሉ ከመ ይደኀሩ በእንተ ድካመ ርስዓን እስመ ኢይትከሀሎ ይጻሙ በከመ ቀዳሚ ዘአመ ውርዛዌሁ እስመ ሥጋዊ ውእቱ ፃማ ገድሎ፤ በኃይለ ነፍስ የሚሠራ አንክሮ ተደም ካልሆነ በቀር ርስዓን ስላመጣው ድካም ጾምን፣ ጸሎትን፣ ሰጊድን፣ ቁመትን በሕፃንነቱ እንደሚሠራው አድርጎ መሥራት አይችልም፡፡ በሕፃንነት ወራት ደክሞ የሚሠራው የትሩፋት ሥራ በኃይለ ሥጋ የሚሠራ ነውና ብሏል፡፡ ተግሳጽ 7

ስለዚህ ኃይለ ሥጋ ጾምን፣ ጸሎትን፣ ሰጊድን፣ ቁመትንና እነዚህን የመሳሰሉትን ቅዱሳት ምግባራት በበለጠ ሊሠራቸው የሚችልበትን የሕፃንነትንና የወጣትነትን ዘመን በከንቱ አሳልፌ ኃይለ ሥጋ በሚደክምበት ጊዜ እነዚህን ሁሉ ምግባራት አከናውናቸዋለሁ ማለት በአዲሱ ሰውነቴ ዓለምን በአሮጌው ሰውነቴ እግዚአብሔርን አገለግላለሁ ማለት መሆኑ እርግጠኛ ነው፡፡

እስከዚያውስ ድረስ ቀጠሮው ያልታወቀ ሞት የመጣ እንደሆነ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ መቅረት አያጸጽትም? ለእውነተኛ ክርስቲያን የተገባ አንዋዋርስ ኃይለ ሥጋ በሚበረታበት በወጣትነት ዘመን ጾምን፣ ጸሎትን፣ ሰጊድን፣ ቁመትን ኃይለ ነፍስ በሚበረታበት በእርጅና ዘመን አንክሮን፣ ተደሞን፣ ተዘክሮተ እግዚአብሔርን አዘውትሮ መገኝት ነው፡፡

ሽማግሌውም ቢሆን በወጣትነቱ ወራት የሠራውን ኃጢአት እያሰበ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብበትን መንፈሳዊ ሥራን ማዘውተር እንጂ በቧልት፣ በዕለት፣ በሐሜት፣ በዘፈን፣ በጨዋታ መካከል ተቀምጦ የሕፃናትን ሥራ ሲሠሩ መገኘት በእግዚአብሔር ዘንድም በሰውም ዘንድ ሊያስከብረው አይችልም፡፡

ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚሁ ሲናገር የዳዊትን ቃል ጠቅሶ እንዲህ ብሏል፡- ወሬዛ ለእመ በጽሐ ኀበ ርስዓን ያእምር ዘይደሉ ለሥርዓተ ልሂቅ ወይበል ኃጢአትየ ዘበንዕስየ ወእበድየ ኢትዝክር ሊተ፤ ጎልማሳ የነበረ ሰው ወደ እርጅና ወራት በደረሰ ጊዜ ሽማግሌ ሊሰራው የሚገባውን ሥራ ማወቅ ይገባዋል፡፡ በሕፃንነቴ ወራት የሠራሁትን ኃጢአት ሰንፌም የሠራሁትን ኃጢእት አታስብብኝ ማለት ይገባዋል፡፡ ወእመሰ አዝለፈ ላዕለ ገቢረ ኃሣር በመዋዕለ ርስዓን ኢይደልዎ ይሰመይ አረጋዌ እስመ ኢይቤ ኃጢአትየ ዘበንእስየ ወእበድየ ኢትዝከር ሊተ፤ በእርጅናው ወራት በሕፃንነቱ ጊዜ ይሠራው የነበረውን ሥራ መላልሶ ከሠራው ኃጢአትየ ዘበንዕስየ ወእበድየ እትዝክር ሊተ ብሎ አልጸለየምና ሽማግሌ መባል አይገባውም፡፡ ተግሣጽ 7

የሆነ ሆኖ ልዑል እግዚአብሔር ወጣትነትንም ሽምግልናንም ዕድል አድርጎ መስጠቱ ዘመናችን በሚተላለፍባቸው በሁለቱም መንፈሳዊ ሥራን ሠርተን እንድንጠቀምባቸው ስለሆነ ስንፍናን በትጋት ማራቅ ለሁላችን የተገባ ነው፡፡

ፈታናን ዕፁብ ዕፁብ ብሎ መንፈሳዊ ሥራን መሥራትን ማቋረጥ ከቶ አይገባም፡፡ ጹሞ በመዋል ሰግዶ ጸልዮ በማደር  የሚፈጸመውና የሚታለፈው ለእኛ የተሰጠንስ አነስተኛው ፈተና ይቆይና ጻድቃን ሰማዕታት ለሞት ለኅልፈት የሚያበቃውን ፀዋትወ መከራ በተቀበሉ ጊዜ ዕፁብ ዕፁብ በማለት የተጋድሎ ሥራቸውን አላቋረጡም፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፈተናን በመሰቀቅ መንፈሳዊ ሥራን ማቋረጥ እንደማይገባን ሊያስረዳን እንዲህ ብሏል፡- ወበእንተዝ ኢንትቁጣዕ እስመ ዘእንተ አፍአነ ብእሲ ይበሊ ወዘእንተ ውስጥነሰ ይትሔደስ ኩሎ አሚረ እስመ ሕማምነ ዘለሰዓት ቀሊል ክብረ ወስብሓተ ብዙኅ አፈድፈዶ ይገብር ለነ፡፡ እስመ ዘኢንሴፎ ዘያስተርኢ አላ ዘኢያስተርኢ እስመ ዘያስተርኢ ኃላፊ ውእቱ፡፡ ወዘሰ ኢያስተርኢ እስከ ለዓለም ውእቱ፤

ስለዚህ እንበሳጭ ቸል እንበል በአፍአ ያለ ሰውነታችን  የሚጠፋ ነውና በውስጥ ያለው ሰውነታችን ግን ሁል ጊዜ ይታደሳልና፡፡ የጥቂት ሰዓት መከራችን ክብርንም፣ ምስጋናንም አብዝቶ ያስደርግልናልና የማይታየውን ነው እንጂ የሚታየውን ዓለም ተስፋ አናደርግምና የሚታየው ዓለም የሚያልፍ የማይታየው ዓለም ግን ለዘለዓለሙ የሚኖር ስለሆነ፡፡ 2ቆሮ 4፡ 17-18

ሊቀ ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲሁ ፈተናን በመሰቀቅ መንፈሳዊ ሥራን ማቋረጥ እንዳይገባ ሲያስረዳ፡- አኃዊነ ኢታንክርዋ ለእንተ ትመጽአክሙ  መከራ ከመ ዘነኪር ግብር ይከውን ብክሙ ዳዕሙ ከመ ትሳተፍዎ በሕማሙ ለክርስቶስ ወተፈሥሑ ከመ አመ ያስተርኢ በስብሐቲሁ ትትሐሠዩ ፍሡሐኒክሙ፡፡  ወእመሶበ ዘተዐየሩክሙ በእንተ ስሙ ለክርስቶ ብፁዓን አንትሙ እስመ ስብሓቲሁ ወኃይሉ ለእግዚአብሔር ወመንፈሱ የዐርፍ ላዕሌክሙ፡፡

ወንድሞቻችን የምትመጣባችሁን መከራ እንግዳ ሥራ እንደሚደረግባችሁ አድርጋችሁ አታድንቁዋት የለመዳችኋት መከራ ናት እንጂ የማትለምዱትም መከራ ይመጣባችኋል፡፡ በመከራ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ በጌትነቱ በተገለጠ ጊዜም ክብሩን አግኝታችሁ ደስ ይላችሁ ዘንድ ዛሬ በመከራው ደስ ይበላችሁ፡፡ ስለ ክርስቶስ ቢሰድብዋችሁ የተመሰገናችሁ ናችሁ፡፡ የእግዚአብሔር ክብሩና ኃይሉ ሀብቱም በእናንተ ያድራልና ብሏል፡፡ 1ጴጥ 4፡ 12-15

ሊቀ ሐዋርያቱ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ቃሉ የነገረን በመከራ ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆናችንን ነው፡፡

በመከራ ወይም በፈተና ከክርስቶስ ጋራ አንድ መሆንን ለማግኘት የምንችል ከሆን ጾም፣ ጸሎት፣ ሰጊድ፣ ቁመት በሚያመጡት ፈተና ላይ ሰውነታችንን መጣልን ለምን እንፈራለን፣ ለምንስ እንሰቀቃለን? ክርስቶስ ያዘዘልንንና የፈቀደልንን ሥራ ሳንሠራ የክርስቲያንነትን ዋጋ ለማግኘት አንችልምና ሰፊውን በር ሰፊውን መንገድ ትተን ወደ ጸባቡ ገብተን መሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነተኛው መንገድ እንከተለው፡፡

አሁን የማስታውቃችሁ ጌታችን ቀድሶ ባርኮ በሰጠን በዚህ በዓቢይ ጾም መዝፈንን፣ መጫወትን፣ መሣለቅን፣ ያለልክ ጠጥቶ እግዚአብሔርን አለማሰብን፣ መጣላትን፣ መቃናትን፣ ማሳጣትን ከሰውነታችሁ አርቃችሁ ቅዱስ ጳውሎስ የመረጣቸውን ቅዱሳት ምግባራት መፋቀርን፣ በመንፈሳዊ አካሔድ ደስ መሰናኘትን፣ አንድነትን፣ መታገሥን፣ መመጽወትን፣ ቸርነትን፣ ሃይማኖትን፣ ቅንነትን፣ ንጹሕነትን ታገኙ ዘንድ ነው፡፡

ከዚህም ቀጥዬ ስለ መላ ኢትዮጵያ ሕይወት ሰላማዊ ኑሮና አንድነት ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የዳዊትን ሀብተ መዊዕ እንዲሰጥልን በየጸሎታችሁ ወደ እግዚአብሔር ታመለክቱ ዘንድ አሳስባችኋለሁ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በረከተ ጾሙን ያሳድርባችሁ፡፡ እሱ በጾሙ ዲያብሎስን ድል እንደነሣው በጾማችሁ ድል እንድትነሡ ኃይሉን ይስጣችሁ መዋዕለ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞና አሳልፎ ብርሃነ ትንሣኤውን ለማየት ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል!

ምንጭ፡ ዜና ባስልዮስ ሊቀ ጳጳሳት ገጽ 92-98

Please follow and like us:
error0
fb-share-icon20

1 thought on “የዐቢይ ጾም ቃለ ምዕዳን በብፁዕ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ባስሊዮስ”

  1. admin says:

    በመከራ ወይም በፈተና ከክርስቶስ ጋራ አንድ መሆንን ለማግኘት የምንችል ከሆን ጾም፣ ጸሎት፣ ሰጊድ፣ ቁመት በሚያመጡት ፈተና ላይ ሰውነታችንን መጣልን ለምን እንፈራለን፣ ለምንስ እንሰቀቃለን? ክርስቶስ ያዘዘልንንና የፈቀደልንን ሥራ ሳንሠራ የክርስቲያንነትን ዋጋ ለማግኘት አንችልምና ሰፊውን በር ሰፊውን መንገድ ትተን ወደ ጸባቡ ገብተን መሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነተኛው መንገድ እንከተለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Post

ማነው እንደ መጻጉዕ ያልታመመ?

ጸሎት እንዴት ተወዳጅ ነገር ነው፡፡ ሥራውስ እንዴት ያማረ ነው፡፡ ጸሎት ከመልካም ሥራ ጋር ሲደረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ በይቅርታ መንፈስም ሲደረግ፤ ወደ ላይ ሲያርግ ሁሉ ይታወቃል፡፡ ከልብ የተደረገ ንጹህ ጸሎት

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

የ፳፻፲፭ ዐቢይ ጾምን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት መልእክት! • በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም ኢትዮጵውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ! እንደ ስሑትና ደካማ ሰብአዊ ባሕርያችን ሳይሆን

ሞትን በሞት የሻረ

በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊምንጭ፡ The Fathers of the Church Patristic Series 91 ጌታችን በሞት ላይ ተረማመደ፡፡ ከሞት ባሻገር ላለ መንገድም መረማመጃን አዘጋጀ፡፡ በሞት መንገድ ሞትን ያለፈቃዱ ያስወግደው ዘንድ በፈቃዱ ለሞት የተገዛ