‹‹ቤተክርስቲያን ያለ ጠባቂ ነበረች መልካም የሆነ ጠፍቶ ክፋት ግን በሁሉ ቦታ ነበር ፡ወቅቱ መብራት በሌለበት ጭለማ እንደመጓዝ ነበር፡፡ ክርስቶስ ተኝቶ የቁስጥንጥንያ ባሕር ለተወሰነ ጊዜ በአርዮሳውያን እጅ ነበር፡፡ በዚህ ያገኘሁት ምንም ወይም በጣም ትንሽ ምዕመን ነው፡፡ እነሱም ያለምንም ክትትል እና ስርዓት የሚኖሩ ናቸው፡፡ በወቅቱ የነበሩ ካህናትም አብዛኞቹ ክህነትን እንደ እንጀራ መብያ እንጂ ለክህነት በሚገባው ክብር እና ልክ የሚሰሩ አልነበሩም፡፡ የነፍስ እረኛ ኃላፊነት ከበጎች እረኛ ኃላፊነት ያነሰ ያህል ነበር ሚሰማቸው›› ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ይህንን የተናገረው የቤተክርስቲያን ወርቃማ ዘመን የሚባለውን የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመንን የቤተክርስቲያን ሁኔታ ሲገልጽ ነበር፡፡ ይህ አባባል ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ በትክክል የሚያስረዳ ይመስለኛል፡፡
የ4ኛው መቶ ክፍለዘመንን የቤተክርስቲያን ሁኔታ በወፍ በረር ከዚህ እንደሚከተለው ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
የክፍለ ዘመኑ የመጀመሪያው ወቅት
በ305 የቅድስት ቤተክርስቲያንን ምእምናንን፣ አባቶችን፣ መነኮሳትን፣ ጳጳሳትን በማሳደድ፣ በማጋዝ እና በመግደል ሰራዊቱን ያሰማራ ከዲዮቅልጥያኖስ ቀጥሎ የነገሰ መክስምያኖስ የሚባል ክፉ ንጉስ ነበር፡፡ ከዚህ ክፉ ንጉስ ተሸሽጎ ቤተክርስቲያንን በስውር ሲያስተዳድር የነበረውን የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስን ስልጣን በመሻማት አምጾ የራሱን ጳጳሳት መሾም የጀመረው ሜሊጢየስ የዚህ ዘመን የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ፈተና ነበር፡፡ ይህ ሰው እስከ ኒቂያ ጉባኤ ድረስ 35 የሚሆኑ የሀሳቡ ተጋሪ የሆኑ ጳጳሳትን ሾሞ ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ከተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ እረፍት (311) በኋላ ብቻ ሳይሆን በኒቂያ ጉባዔ ከተወገዙ እና ከታገዱ በኋላም ጭምር ለቅድስት ቤተክርስቲያን ፈተና መሆናቸውን ቀጥለው ነበር፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያን ያለ ስልጣናቸው ቤተክርስቲያንን ሊከፍሉ የተነሱትን ሜሊጢየሳውያን በኒቂያ ጉባኤ 4ኛው አንቀጽ ላይ ያወገዘቻቸው ሲሆን ወደፊትም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የዚህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙትን በተመሳሳይ የተወገዙ እንደሆኑ በቤተክርስቲያን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የኒቂያ ጉባዔ ወስኗል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ላይ ከቤተክርስቲያን ጠቅላላ ሲኖዶስ እውቅና ውጭ የሚደረግን የጵጵስና ሲመትም አውግዟል፡፡ (የኒቂያ ጉባኤ ውሳኔ የሆኑትን 20 ውሳኔዎች በአስራት ገብረማርያም ትምህርተ መለኮት መጽሐፍ ላይ ይመልከቱ)
ሌላው የዚህ ዘመን ፈተና የነበሩት ኖቫቲያን ይባላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ቤተክርስቲያን በስደት ወቅት በነበረችበት ወቅት ለጥቅማቸው ሲሉ ቤተክርስቲያንን፣ የቤተክርስቲያን አባቶችን አሳልፈው የሰጡ እና ሃይማኖታቸውን ጭምር በመካድ ከሞት የተረፉ ሰዎች፣ ቤተክርስቲያን ሰላም ያገኘች ሲመስላቸው ወደ ቤተክርስቲያን በመመለስ በቀደመ ክብራቸው እና ስራቸው መኖር የሚሹትን ቤተክርስቲያን በምትፈልጋቸው ወቅት የከዷት ከሃዲያን ናቸውና ቤተክርስቲያን በንሰሃ ጭምር ልትቀበላቸው አይገባም፡፡ ከእነርሱ ጋር ከምናገለግል ብንለይ ይሻላል በማለት ለቤተክርስቲያን በመቆርቆር የራሳቸውን ጳጳሳት በመሾም ከቤተክርስቲይን መርህ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ናቸው፡፡
3ኛው ወገን አርዮስ እና የአርዮስ ተከታዮች ሲሆኑ እነዚህ ወገኖች ቤተክርስቲያንን በሁለት ወገን ሲያስጨንቋት ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጌታችንን ክብር ይግባው እና ፍጡር ነው በሚል አስተምህሮዋቸው ሲያስጨንቋት በሌላ መልኩ ደግሞ ከመንግስት ጋር ያላቸውን ቀረቤታ በመጠቀም ይህንን ሀሳባቸውን የሚቃወሙትን ኦርቶዶክሳውያን አባቶችን በያሉበት እንዲሰደዱ፣ እንዲጋዙ ሲብስም እንዲገደሉ እያስደረጉ ቤተክርስቲያንን መከራ ሲያሳዩ የነበሩ ወገኖች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች በተለይ አርዮሳዊ የሆነ ንጉስ በሚሾምበት ወቅት ሰራዊቶቻቸውን ጭምር በየቦታው፣ በየገዳማቱ በማሰማራት ለቤተክርስቲያን ትንፋሽ እስኪያጥራት ድረስ እጅግ ያስጨንቋት ነበር፣ እንደ እግዚአብሔር ቸርነት ባይሆን ቤተክርስቲያን ያንን ወቅት ለማለፍ ባዳገታት ነበር፡፡
በዚህ ዘመን የተነሳው ታላቁ ሐዋርያዊው የሚባለው አባታችን ቅዱስ አትናቴዎስ እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውን መግፍኤዎች በሙሉ ብቻውን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ተሸክሞ፣ የኒቂያ አባቶችን ውሳኔ አስጠብቆ ሲያስፈልግ እያብራራ ወደ ሚቀጥሉት ተረካቢ የቤተክርስቲያን አባቶች ወደ ቀጶዶቂያ ቅዱሳን ለማስተላለፍ ሞክሯል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ይህንን ሲያደርግ አምስት ጊዜ ከመንበሩ እየተሰደደ፣ ለ15 ዓመት ቤተክርስቲያንን በስተደት ሆኖ ሲመራ፣ ምዕምናንን ሲያረጋጋ፣ እንዲሁም ለመናፍቃኑ ተገቢውን መልስ ሲስጥ እና የኒቂያ ጉባዔን ውሳኔ ሲያብራራ፣ ለነገስታቱም ቤተክርስቲያንን ያለ አግባብ እያሳደዷት እንደሆነ በደብዳቤ ሲያሳውቅ ኖሯል፡፡
በዚህ ዘመን በመንግስት አማካይነት በመነኮሳት ላይ የተደረገውን ግድያ ለማሳየት፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት ስለ ቅዱስ አትናቴዎስ በጻፈው በ23ኛ ስብከቱ አንድ ቦታ ላይ እንዲህ በማለት ይናገራል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ከሚያሳድደው ንጉስ ሸሽቶ በአንድ ገዳም መደበቁን የተረዳው ንጉስ ነፍሰ-ገዳይ ወታደሮቹን ወደዛው ይልካቸዋል፡፡ እነርሱም እዛ ሲደርሱ ቅዱስ አትናቴዎስን አሳልፈው እንዲሰጡ ያለበለዚያ በሱ ፋንታ እንደሚገደሉ ያስፈራራቸዋል፡፡ እነርሱም አባታችንን አሳልፈን ከምንሰጥ ሞትን እንመርጣለን ብለው በወታደሮቹ ሰይፍ ብዙዎቹ ያልቃሉ፡፡ ይህንንም ሁኔታ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል
‹‹ለክርስቶስ የመሞትን ያህል የተደበቀበትን ከመናገር ስለ እርሱ ሰማዕት ሆኑ፡፡ ለእርሱ መሞትን ከገዳማዊ የጽሞና ሕይወት፣ አብዝቶ ከመጾም እና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ከሚገኝ እራስን መግዛት በላይ ክብር እንዳለው ዋጋ ሰጡት፡፡››
በዚህ ዘመን ቅድስት ቤተክርስቲያን ከነ ድዮቅልጥያኖስ፣ ከነ መክስምያኖስ መከራ እና ስደት በደጉ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ አማካይነት ከ313 ዓ.ም ጀምሮ ብታርፍም፣ ከውስጧ በተነሱ ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል በተነሱ ሰዎች እና በነዚህ ሰዎች አማካይነት ቤተክርስቲያንን በሚጠሉ ነገስታት ምክንያት ቤተክርስቲያን እንዳታርፍ ሆና መከራን ስትገፋ ኖራለች፡፡
ዛሬም ቅድስት ቤተክርስቲያንን እንደ ሜሊጢያስ በጎሳ የተከፈለ ሲኖዶስ በመፍጠር ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ ውጭ ጳጳሳትን በመሾም ቅድስት ቤተክርስቲያንን ሊከፍሏት የሚሹ የዘመናችን ሜሊጢየሳውያን ድርጊታቸው በኒቂያ ጉባኤ አባቶች የተወገዘ መሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡
እንዲሁም እንደ አርዮሳውያን የመንግስትን ኃይል ተገን አድርገው የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን የሚያሳድዱ፣ የሚገድሉ የመንግስት ተላላኪ የውስጥ ባንዳዎች እንዳሉት ሁሉ የተመረጡበትን ኃላፊነት ያልዘነጉ፣ የስልጣን፣ የዘር፣ እና የገንዘብ በሽታ ያላሸነፋቸው ጥቡዐን አባቶች መኖራቸው በእግዚአብሔር ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደርገናል፡፡
የክፈለ ዘመኑ ሁለተኛው ክፍል
ከቅዱስ አትናቴዎስ በኋላ በተነሱት በቀጶዶቂያ አባቶች ዘመንም (ቅዱስ ባስልዮስ ዘዐምድ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ) መከራው በዝቶ ቅድስት ቤተክርስቲያንም አሰከፊ ሁኔታውስጥ ነበረች፡፡ ዘመኑንም ነባቤ መለኮት በቁስጥንጥንያ በነበረበት ወቅት እንዲህ በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹ቤተክርስቲያን ያለ ጠባቂ ነበረች መልካም የሆነ ጠፍቶ ክፋት ግን በሁሉ ቦታ ነበር ፡ወቅቱ መብራት በሌለበት ጭለማ እንደመጓዝ ነበር፡፡ ክርስቶስ ተኝቶ የቁስጥንጥንያ ባሕር ለተወሰነ ጊዜ በአርዮሳውያን እጅ ነበር፡፡ በዚህ ያገኘሁት ምንም ወይም በጣም ትንሽ ምዕመን ነው፡፡ እነሱም ያለምንም ክትትል እና ስርዓት የሚኖሩ ናቸው፡፡ በወቅቱ የነበሩ ካህናትም አብዛኞቹ ክህነትን እንደ እንጀራ መብያ እንጂ ለክህነት በሚገባው ክብር እና ልክ የሚሰሩ አልነበሩም፡፡ የነፍስ እረኛ ኃላፊነት ከበጎች እረኛ ኃላፊነት ያነሰ ያህል ነበር ሚሰማቸው››
እነዚህ አባቶች በቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በነበረው በዓለማዊው ትምህርትም ልሂቃን ነበሩ፡፡ ከቅድስት ቤተክርስቲያን ውጭ ባሉት ዐለማውያን ትምህርት ቤት ውጭም ጭምር በመምህርነት የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡
በዚህ ዘመን የነበረው ከእነርሱ ጋር በዓለማዊ ትምህርት ይማር የነበረው የዛሬው ክፉ ንጉስ ቫለንስ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መምህራን በዓለማዊው ትምህርት ቤት እንዳያስተምሩ አዋጅ አወጣ፡፡ ከዛ አልፎ በቅዱስ ባስልዮስ ይተዳደር የነበረውን የቂሳርያ ሀገረ ስብከት ለሁለት ከፍሎ አንዱን ከቅዱስ ባስልዮስ አስተዳደር ውጭ ለማድረግ እና ቤተክርስቲያንን ለማዳከም ስራ ጀመረ፡፡ አልፎ ተርፎም ነባቤ መለኮት ስለቅዱስ ባስልዮስ በጻፈበት በ42ኛ መልእክቱ እንደሚነግረን ቅዱስ ባስልዮስን የሚያስፈራራ ወንበዴ መልእክተኛ ከንጉሱ ወደ እርሱ ተላከ፡፡ መልእክተናውም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ መጥቶ
‹‹ያለህን ሁሉ ንብረት ወርሼ፣ ሞትን እስክትጠላ ደብድቤ ወደ ሌላ ቦታ አግዝሃለሁ›› በማለት ዛተበት፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ‹‹ከእኔ ሚወረስ ምንም ሀብት የለም፡፡ ሀብቴ መጽሐፎቼ እና የለበስኳት መጎናፀፊያ ነች፡፡ ደብድቤ ለምትለውም እኔ ብዙ ዱላ ሚያሻኝ ሰው አይደለሁም፡፡ እስትንፋሴ በአንድ ምት ፀጥ ትላለች፡፡ ይሄም በፍጥነት ወደምናፍቀው ወደጌታዬ ያደርሰኛል፡፡ በዚህም ታላቅ ውለታን ትውልልኛለህ፣ ወዴሌላ ቦታ አግዝሃለሁ ለምትለውም እኔ መነኩሴ ነኝ፡፡ በየትም ቦታ ብኖር ይስማማኛል›› በማለት የዛሬ አባት ተብዬዎችን ጭምር የሚያርደውን ዛቻ ውሃ ቸለሰበት፡፡
በጣም የሚገርመው ቅዱስ ባስልዮስ ደሃ ሆኖ የተወለደ ወይም እንደዛሬ አባቶች በአጋጣሚ ሀብት ያገኘ ግለሰብ አልነበረም፡፡ በጣም ከሀብታም ቤተሰብ የተወለደ ያለውንም ሀብት በሀገሩ በተነሳ ድርቅ ምከንያት ወገኖቹ በረሃብ እንዳይሞቱ እነርሱን የታደገበት፣ እጓለማውታን ያቋቋመበት፣ ሽማግሌዎች የሚጦበት፣ ሕመምተኞች የሚታከሙበት፣ እንግዶች የሚያርፉበት ገዳም የመሰረተበት፣ በዐለማዊውም በመንፈሳዊው እውቀቱም ምስጉን የነበረ አባት ሲሆን ሀብትን ከሰሩ የሚያውቅ ለሀብት እንደአሁን አንዳንድ አባቶች የማይነሰፈሰፍ ቅዱስ አባት ነበር፡፡
የተከፋፈለ ግዛቱንም ለማስጠበቅ በዛ የሚያምናቸውን ወዳጆቹን እየሾመ ቤተክርስቲያንን ሲጠብቅ ኖረ፡፡ በዘመኑ የነበረውን የክህነት አሰጣጥ ብልሽት እና አቅም በማስተማር ለማስተካከል ሞከረ የድካሙን ፍሬ በ381 በተደረገው ጉባኤ ሳይመለከት ከዚህ ዐለም እንግልት በ379 በእረፍት ቢለይም የእርሱ ደቀመዛሙርት እና ወንድሞች የሆኑት ሁለቱ አባቶች ህልሙን ከዳር አደረሱለት፡፡
በዚህ ዘመን ለነበረው የቅዱሳን አባቶች ተጋድሎ እውነትን አስተውሎ ከእውነት ጎን የቆመው እና በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ከስደት ነጻ የወጣቸውን ቤተክርስቲያን በኒቂያ ጉባዔ ሃይማኖት እንድትወሰን ያደረገው ኦርቶዶክሳዊው ንጉስ ቴዎዶስዮስ ውለታ አይረሳም፡፡ አባቶችም ቆስጠንጢኖስ ቤተክርስቲያንን ነጻ አወጣ ቴዎዶስዮስ ደግሞ ኒቂያዊት (ኦርቶዶክሳዊት) አደረጋት ብለውለታል፡፡
ዛሬም ቤተክርስቲያን እንደ ንጉስ ቴዎዶስዮስ ቤተክርስቲያንን በሰሜን እና በደቡብ ከውስጥ የሚከፍሏትን ወገኖች እየደገፈ ቤተክርስቲያንን የሚከፍላትን ሳይሆን የቤተክርስቲያንን እውነት ተረድቶ ለቤተክርስቲያን እና ለሀገር አንድነት የሚሰሩትን እውነተኛ ቅዱሳን አባቶችን የሚሰማ የሚያግዝ ንጉስ ትፈልጋለች፡፡ ወይ ያለውን ንጉስ ልቡን እንዲቀይርላት ወይም ደግሞ የተሻለ ሌቤተክርስቲያን እና ለሀገር አንድነት ሁሉንም በየሃይማኖቱ የሚያግዝ ንጉስ ቴዎዶስዮስን ይላክላት፡፡
እንደ ቅዱስ ባስልዮስ እና ጎርጎርዮስ በመንፈሳዊነት፣ በአስተዳደር፣ በእውቀት ስል የሆኑ፣ ለመንግስታት ዛቻ እና ድንፋታ የማይንበረከኩ፣ የእረኝነት ኃላፊነቱ እራስን ጭምር አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ መሆኑን የሚገነዘቡ፣ ሥርዐተ ቤተክርስቲያን እንዳይጠፋ ካህናት የተማሩ እና ለእንጀራ ብቻ ሳይሆን የነፍስና የስጋ ኃላፊነት ያለባቸው ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ስልጣንን የጨበጡ መሆናቸውን ሊረዱ በዚህ መርህም ጭምር ሊኖሩ ይገባል፡፡
የነዚህ ቅዱሳን አባቶች እና ደጋግ ነገስታት በረከት ይደርብን፡፡ የነዚህ ቅዱሳን አማላክ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ጌታ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ይጠብቃት፡፡ አሜን
ይህ ጽሑፍ ጠሚ አቢይ አህመድ በመጋቢት 2016 ዓ.ም የቅድስት ቤተክርስቲያንን አባቶች ሰብስበው ሲያወያዩ ከአንዳንድ አባቶች ከነሱ በማይጠበቅ ክብር ቤተክርስቲያንን አሳንሶ አኮስሶ መንግስት ቤተክርስቲያን ላይ የሚያደርሰውን በደል ባላየ ሲያወድሱት ከቀደሙ አባቶች ሕይወት ብንማር በማለት የተጻፈ ነው፡፡