+251-993-818276 akofeda@gmail.com Addis Ababa, Ethiopia

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

የ፳፻፲፭ ዐቢይ ጾምን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት መልእክት!

• በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም ኢትዮጵውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ! እንደ ስሑትና ደካማ ሰብአዊ ባሕርያችን ሳይሆን እንደ አባታዊ ቸርነቱ ሁል ጊዜ በምሕረቱ የሚጐበኘን አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዐቢይ ጾም አደረሰን፤ አደረሳችሁ!

• “ንጹም ጾመ፣ ወናፍቅር ቢጸነ፣ እስመ ከማሁ አዘዘነ፤ ጾምን እንጹም፤ ባልንጀራችንንም እንውደድ፣ እንዲህ አዞናልና” (ቅዱስ ያሬድ)

እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ስንኖር እንድናደርገው ያዘዘን ዐቢይ ነገር ቢኖር ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ እየመገበ የሚገኘው በፍቅር ነው፡፡ እኛንም ከፍዳ ኃጢአት ያዳነን በፍቅር ነው፤ ሕይወታችንና ንብረታችን ተጠብቆ የሚኖረው ፍቅር ሲኖር ነው፡፡

ግላዊና ማኅበራዊ ኑሮአችን እንዲሁም ሃይማኖታዊ አምልኮአችንና የተግባር እንቅስቃሴአችን በሙሉ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ፍቅር ሲኖር ነው፡፡

በፍቅር ውስጥ በረከት እንጂ ጉድለት የለም፤ በፍቅር ውስጥ ጤና እንጂ በሽታ የለም፤ በፍቅር ውስጥ ጽድቅ እንጂ ኃጢአት የለም፤ በፍቅር ውስጥ እግዚአብሔር እንጂ ዲያብሎስ የለም፡፡ ይህም በመሆኑ ቅዱስ መጸሐፍ ፍቅርን ‹‹የሁሉም ነገር ማሰሪያ ነች›› በማለት ይገልጻታል፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሁሉም የምትበልጠው ታላቋ ትእዛዝ ‹‹ፍቅር›› እንደሆነች ከመግለጹም በላይ ኦሪትና ነቢያት ሁሉ በእርሷ እንደሚጠቃለሉ አስተምሮናል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

ፍቅርን እንደ ዓይን ብሌን ስንጠብቃት በእጅጉ የምትጠቅመንን ያህል ስንተዋት ደግሞ በእጅጉ ትጎዳናለች፡፡ በፍቅር እጦት የሚደርሰው ጉዳት በተወሰነ ነገር ብቻ ሳይሆን በነፍስም ሆነ በሥጋ፣ በምድርም ሆነ በሰማይ እጅግ በጣም የገዘፈና የሰፋ ነው፡፡

በሀገራችን የሆነውና እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ ፍቅርን ባጣንባቸው ዓመታት ከየት ወዴት እንደደረስን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚገነዘበው ነው፡፡ ያተረፍነው ነገርም ምን እንደሆነ የምናውቀው ነው፡፡

ይሁንና የፍቅር እጦት ምን ያህል እንደጎዳን ራሳችን ተገንዝበን ወደ ሰላሙ መንገድ መመለሳችን የተሻለ አማራጭ መሆኑን ሳንመሰክር አናልፍም፡፡ የተጀመረው የፍቅርና የሰላም ጉዞም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ልባዊ ምኞታችንና ጸሎታችን ነው፡፡

ይህንን ሰላም እንዲመጣ ያደረጉ ወገኖችም ሁሉንም ሳናመሰግን አናልፍም፡፡ ምክንያቱም በሰዎች መካከል ፍቅርንና ሰላምን የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች እንደሚባሉ ጌታ እንደ አስተማረን ብፅዕና ይገባቸዋልና ነው፡፡ (ማቴ.፭፥፱)

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

የፍጹም ፍቅር መገኛ የሆነው ቅዱስ ወንጌል የሚያስተምረው ፍቅር ራስን ማፍቀር ወይም መውደድ ሳይሆን ራስን መጥላት ባልንጀራን ግን መውደድ እንደሆነ ነው፡፡ “ወንጌላዊ-ፍቅር ፍጹም ነው” የሚያሰኘውም ቅሉ ይህ ነው፡፡

ለሁለት ሺህ ዘመናት ያህል በቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ ላይ የተገነባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ባህልም ይህን ፍቅር ጠብቆ የሚጓዝ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ አበው መነኮሳት ከነበራቸው ፍቅርና ትሕትና የተነሣ፣ የሹመት ሽሚያ አያውቁም ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ትልቁን ሥልጣን ይቅርና የአንድ ገዳም መሪ ለመሆንም በእግር ብረት ታስረው በግድ ካልሆነ በቀር እሺ ብለው በፈቃደኝነት ሹመትን አይቀበሉም ነበር፡፡

ራሱን በራሱ መሾም ወይም እኔን ሹሙኝ ብሎ መናገርና የሌላን ድጋፍ መጠየቅ ለኢትዮጵያውያን መነኮሳት ጭራሽ ነውርና ጸያፍም ነበር፡፡ ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ ለሦስት ሺህ ዘመናት የዘለቀው ሃይማኖታችን ምንም ዓይነት መለያየት ሳያጋጥመው አንድ ሆኖ ሊዘልቅ የቻለው ያም በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ጠንካራ አንድነት ለሕዝቡም በመትረፉ የሀገሪቱን አንድነትና ነጻነት አስጠብቆ እስከ ዘመናችን ሊደርስ ችሎአል፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን የሕዝብንና የሀገርን አንድነትና ነጻነት ለማስጠበቅ ያደረገችውና የምታደርገው ጥረት ሊያስመሰግናት እንጂ ሊያስወቅሳት አይገባም፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

ከቅርብ ቀናት ወዲህ በቤተ ክርስቲያናችን ተከሥስቶ የነበረውን ሕጋዊ ያልሆነ ድርጊት የቤተ ክርስቲያናችንን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና ባሕላዊ መርሕን የናደ፣ እንደዚሁም በኢትዮጵያ ይቅርና በዓለም ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ድርጊት እንደሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

ይህንን የቤተ ክርስቲያን ድምፅ በመስማትና በመቀበል ሕዝበ ክርስቲያንና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለእግዚአብሔር ባቀረቡት ኀዘንና ጸሎት እንደዚሁም ባደረጉት መጠነ ሰፊና ዙርያ መለስ የሆነ የድጋፍ ርብርብ ስሕተቱ ሊታረም ችሏል፡፡

ለተገኘው መንፈሳዊ ውጤትም ጠቅላይ ሚንስትርና መንግሥታቸውን፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሉዓላዊነት እንዲከበር ከፍተኛ መሥዋዕትነት ለከፈለው መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲሁም ይህ ስሕተት እንዲታረም ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን ተሰልፈው ድምፃቸውን ላሰሙ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርብላቸዋለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ግልጽ ማድረግ የምንፈልገው ከቤተ ክርስቲያናችን ዶግማ፣ ቀኖና እና ሥርዓት መከበር እንደዚሁም ከሉዓላዊ አንድነቷ መጠበቅ በመለስ ያለው ጥያቄ ለማስናገድ ቤተ ክርስቲያናችን ዝግጁ መሆኗን ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ሕዝቦች በቋንቋቸው የመማር፣ የማስተማርና የማምለክ እንዲሁም የመተዳደር መብትን ካሁን በፊትም፣ አሁንም፣ ካሁን በኋላም የምትነፍግበት መሠረት እንደሌለም ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡

ይህም በመሆኑ በቋንቋ የመጠቀም መብት በሕገ ቤተ ክርስቲያናችን ምዕራፍ ፪ አንቀጽ ፭ ከቁጥር ፩ እስከ ፫ ባለው አንቀጽ በሚገባ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በቋንቋ የመጠቀም ጥያቄ በሕግ ደረጃ ተመልሶ በተግባር እየተሠራበት የሚገኝ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡ የ

ተወዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

ዛሬ ታላቁን ጾም በፍቅር ሆነን የምንጾምበት ወቅት ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ጾም ማለት ሥጋዊ ፈቃድን በመግታት ከእግዚአብሔር ጋር ጥብቅ ግንኙነት ለማድረግ የሚካሄድ መንፈሳዊ ተጋድሎ ነው፡፡ በጌታችን ጾም በተግባር እንዳየነው ጾም ማለት ዲያብሎስ የሚሸነፍበት በአንጻሩ ደግሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ አሸናፊዎች የሚሆኑበት ኃይል ነው፡፡

ስለሆነም ጾም የተጋድሎና የሙዓት ሜዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የምንታገለውም ልብሰ ሥጋ ሰውን ሳይሆን ረቂቅ ፍጡር የሆነው ሰይጣን በሰው አድሮ የሚነዛውን አጥፊ ሐሳቡንና ድርጊቱን ነው፡፡ ከዚህም ጋር ሰውነታችን ለዚህ ክፉ መንፈስ ታዛዥ እንዲሆን የሚገፋፉ ጥሉላት መባልዕትን መተው፣ ኃይለ ሥጋን መቈጣጠር፣ ኃይለ መንፈስን ደግሞ ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡

በጾም ወቅት የተራቡትን ማጉረስ፣ የታረዙትን ማልበስ፣ የተበደሉትን መካስ፣ ፍትሕና ርትዕ በማኅበረ ሰብ ውስጥ ማንገሥ ያስፈልጋል፡፡በጾም ወቅት ኅሊናችን ማሰላሰል ያለበት ሰው ምን አለ? ወይም ምን አደረገ? በሚለው ሳይሆን እግዚአብሔር በፊቱ ምን ዓይነት ሰው እንድንሆንለት ይፈልጋል? በሚለው ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ጾማችን በዚህ መንፈስ የተቃኘ ፍቅረ፣ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን ማእከል ያደረገ፣ መጠራጠርንና አለመተመማንን ያስቀረ፣ የተለያዩትን ያቀራረበ፣ የተሳሳቱትን ያረመ በአንጻሩ ደግሞ ሁላችንን በሰላምና በፍቅር አንድ አድርጎ ያስተሳሰረ ይሆን ዘንድ በዚህ መንፈስ ተነቃቅተን እንድንጾመው አባታዊ ጥሪያችንን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም በሀገራችን እየታየ ያለው የሰላም ጭላንጭልና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ዝንባሌ ለሁለንተና ልማታችንና ለዕድገታችን እንደዚሁም ለተሟላ አንድነታችን ጠቃሚነቱ የጎላ ስለሆነ እግዚአብሔር ለዘለቄታው እንዲያሳካልን ከልብ እንድናዝንና ወደ አምላካችን በተመሥጦ እንድንጸልይ በአጽንዖት በማሳሰብ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የጾም ወራት ያድርግልን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስምወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Please follow and like us:
error0
fb-share-icon20

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Post

የዐቢይ ጾም ቃለ ምዕዳን በብፁዕ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ባስሊዮስ

ብፁዕ አባታችን በነበሩበት ወቅት ለኢትዮጵያ ሀገራችን እና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ብዙ አስተዋጽኦዎችን ያደረጉ ሲሆን በተለይ በሚመለከተቻው የመንፈሳዊ አገልግሎት ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ከማሳነጽ ጀምሮ በተለያዩ አድባራትና ገዳማት በመዞር አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎችን አድርገዋል፡፡

የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና የመንግስት ባለስልጣናት ግንኙነት

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከስነ ምግባር ጉድለት እና ከእምነት ጋር በተያያዘ ለረዥም ጊዜ ከባለስልጣናት ጋር ሲታገል ኖሯል፡፡ ከመንግስት ጋር መሞዳመድ የሚባል ነገርንም አያውቅም፡፡ በተለይ በቁስጥንጥንያ እያለ አብዝቶ ስለነዚህ

በ 325 በኒቂያ ጉባኤ የተደረጉ ቀኖናዊ ዉሳኔዎች

በአርዮስ የምንፍቅና ትምህርት ምክንያት በ325 ዓ.ም በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ዘመን ቤተክርስቲያን የመጀመሪያወን ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ 318 ብጹዐን አበው በተሰበሰቡበት አደረገች፡፡ አርዮስን ከማውገዝ እና የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ በባህርይ ከአብ ጋር አንድ መሆኑን