+251-993-818276 akofeda@gmail.com Addis Ababa, Ethiopia

አርዮስ እንዴት ሞተ

ይህ መልእክት ቅዱስ አትናቴዎስ ለግብጽ ጳጳሳት እና በአንድ ወቅት ለእስክንድርያ ትምህርት ቤት የበላይ ለነበረው ለቴሙሱ ቅዱስ ሴራፕዮን የጻፈው ነው፡፡

ቅዱስ አትናቴዎስ ይቀጥል፤

የአርዮስን የአሟሟት ሁኔታ እንድገልጽላችሁ ጠይቃችሁኝ ነበር……….በሱ ሞት የምደሰት የሚመስላቸው ሰዎች ይኖራሉ ብዬ በመስጋት ለረዥም ጊዜ ከራሴ ጋር ስወዛገብ ቆይቻለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አርዮስን ቤተክርስቲያን ከተቀበለችው በኋላ ነው የሞተው የሚል ንትርክ በመካከላችሁ እንዳለ ስሰማ፤ በአሟሟቱ ላይ ያለው ንትርክ ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ የአሟሟቱን ሁኔታ መግለጽ እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡ እኔም ይህንን በማሳወቄ በዚህ ጉዳይ ሚከራከሩ ሰዎች ዝም እንደሚሉ ተስፋ አድርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም የአሟሟቱ ድንቅነት በሰዎች ዘንድ ተገልጾ ሲታወቅ፣ ቀድሞ የአሟሟቱን ሁኔታ ይጠራጠሩ የነበሩ የአርዮሳውያን ምንፍቅና በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል የተጠላ እንደሆነ ያለጥርጥር ይገነዘባሉና፡፡

በወቅቱ እኔ በቁስጥንጥንያ አልነበርኩም፡፡ በወቅቱ እዛ ከነበረው እና ይህንን ሁኔታ በዐይኑ ከተመለከተው ከመቃርዮስ ነው የሰማሁት፡፡ አርዮስ በኒቆሞዲያው አውሳብዮስ (በአርዮሳዊነቱ ከአርዮስ ጋር ተወግዞ ተግዞ የነበረ በኋላ ከአርዮስ ጋር ለአፋቸው ምህረት ጠይቀው የኒቂያ ጉባኤን ውሳኔ ተቀብለናል ብለው ለንጉሱ ባቀረቡት ልመና ከግዞት የወጡ ናቸው) ሽምግልና በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ተጋበዘ፡፡ ንጉሱ ጋር በቀረበ ጊዜ፣ ንጉሱ በኒቂያ የተወሰነውን የሃይማኖት አስተምህሮ ተቀብሎ እንደሆነ ጠየቀው፤ አርዮስም የተወገዘበትን ነገር መቀበሉን በትክክል ሳይገልጽ በመሐላ ትክክለኛውን የቤተክርስቲያን እምነት እንደተቀበለ በጽሑፍ አስደግፎ ለንጉሱ አቀረበ፡፡

እለእስክንድሮስ እሱን ያወገዘበትን እምነቱን እንደተወ በመሃላ ለንጉሱ ሲገልጽ ንጉሱም ‹‹ሃይማኖትህ ትክክል ከሆነ በመሃላ በመግለጽህ ደግ አደረክ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን ሳትፈራ በሐሰት ይህን መሀላ ምለህ ከሆነ፣ እግዚአብሔር እንደ መሐላህ ይፍረደብህ›› በማለት ተናገረው፡፡

ከንጉሱ ጋር ሲወጣ አውሳብዮስ እና ተከታዮቹ፣ በተለመደው አመጻቸው ወደ ቤተ መቅደስ ሊያስገቡት ፈለጉ፡፡ ነገር ግን በረከቱ ከእኛ ጋር ይሁን እና የቁስጥንጥንያው ጳጳስ እለእስክንድሮስ፣ ‹‹የምንፍቅና አባቷ፣ ለቅዱስ ቁርባን የተገባ አይደለም እና አልቀበለውም›› ብሎ ተቃወመ፡፡ አውሳብዮስ እና ተከታዮቹም፣ ‹‹ከምኞትህ ውጭ በንጉስ እንዲጋበዝ እንዳደረግነው ሁሉ፣ ነገ (ዕለቱ ሰንበት ነው ሚሆነው) አሁንም ከፍቃድህ ውጭ በዚህ ቤተክርስቲያን ከእርዮስ ጋር ቅዱስ ቁርባንን እንደምንቀበል እወቅ›› በማለት ዝተውበት ሄዱ፡፡

የአርዮሳውያን ሴራ እና የእለእስክንድሮስ ጸሎት

እለእስክንድሮስ ይህን ከሰማ በኋላ አብዝቶ ተጨነቀ፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በመንበርከክ እጁን ዘርግቶ መጸለይ ጀመረ፡፡ መቃርዮስም አብሮት እየጸለየ ነበር፡፡ እናም በጸሎቱ ሁለት ነገርን ፈጣሪውን ለመነ፡፡ ‹‹ነገ አርዮስ የሚስጢራቱ ተካፋይ የሚሆን ከሆነ፣ እኔን ባርያህን አሰናብተኝ፡፡ ሐጥኡም ጻድቁም አብረው አይጥፉ፡፡ ነገር ግን አንተ ቤተክርስቲያንህን የምትታደግ ከሆነ (እንደምትታደጋት አውቃለሁ)፣ ወደ አውሳብዮስ እና ተከታዮቹ ንግግር ተመልከት፣ ቤትህንም ለጥፋትና ለውርደት፣ ለመዘባበቻነት አሳልፈህ አትስጥ›› አርዮስን አስወግደው፣ ያለበለዚያ እሱ ወደ ቤተ መቅደስ ከገባ ምንፍቅናም አብሮት ይገባል፤ እናም እርኩሰትም እንደ ጽድቅ ይቆጠራል፡፡

ጳጳሱ ከጸሎቱ በኋላ በድካም ቁጭ ባለበት፣ ዕጹብ ድንቅ ነገር ተፈጠረ፡፡ አውሳብዮስ እና ተከታዮች በሚዝቱበት ወቅት ጳጳሱ በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ በአውሳብዮስ እና በተከታዮቹ በመተማመን የማይገባ ነገር ይናገር እና ያደርግ የነበረው አርዮስ በተፈጥሮ ጥሪ ወገቡን ይፈትሽ ዘንድ ተለያቸው፡፡ በመጽሐፍ እንደተገለጸው፤ በድንገት ‹‹በግንባሩ ተደፍቶ ለሁለት ተሰንጥቆ ፈንድቶ ሞተ (Falling headlong he burst asunder in the midst)›› በዚህ ሁኔታ ሕይወቱ በማለፉ ከቅዱስ ቁርባንም ከሕይወቱም ሳይሆነ ቀረ፡፡

እግዚአብሔርም በአውሳብዮስ እና ተከታዩቹ ዛቻ፤ እንዲሁም በእለስክንድሮስ ጸሎት መካከል ፍርዱን አደረገ፡፡ ለቅዱስ ሥጋውና ለክቡር ደሙ ስለማይገቡ በውግዘት አርዮሳውያንን በዚህ መልኩ ለየቻው፡፡ ምንም እንኳን የንጉስን እና የሰዎችን ድጋፍ ቢያገኝም በቅድስት ቤተክርስቲያን ግን ውጉዝ መሆኑን እግዚአብሔር በፍርዱ ገለጠ፡፡

የቅዱሳን አባቶችን ጸሎት ሰምቶ ፍርዱን ያደረገ እግዚአብሔር ዛሬም የአባቶቻችንን ፀሎት ሰምቶ ፍርዱን ይፍረድ፡፡ በንጉስ ድጋፍ እና ኃይል እንዲሁም በታጠቁት መሣሪያ ተማምነተወ ቅድስት ቤተክርስቲያንን በሚያስፈራሩትና በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት መካከል እርሱ ፍርዱን ያድርግ

ምንጭ NPNF2 4: 564-565

Please follow and like us:
error0
fb-share-icon20

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Post

መድኃኔዓለም ክርስቶስ

በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ምንጭ፡ The Fathers of the Church Patristic Series 91 ለሟች ሁሉ የሕይወት ምንጭ ይሆን ዘንድ የሟች አዳምን ሥጋ ለለበስክ ለአንተ ክብር ይገባሃል፡፡ አንተ፤ ብዙ ፍሬ አፍርታ እንድትበቅል፣

ሞትን በሞት የሻረ

በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊምንጭ፡ The Fathers of the Church Patristic Series 91 ጌታችን በሞት ላይ ተረማመደ፡፡ ከሞት ባሻገር ላለ መንገድም መረማመጃን አዘጋጀ፡፡ በሞት መንገድ ሞትን ያለፈቃዱ ያስወግደው ዘንድ በፈቃዱ ለሞት የተገዛ

ሲዖልን መሸጋገሪያ

ሁሉን ከምትሰለቅጠው ሲዖል በመስቀሉ ሰውን ወደ ሕይወት ያወጣው የጥበበኛው አናጺ ልጅ እነሆ፡፡ በዛፍ ምክንያት ወደ ሲዖል የወረደው የሰው ልጅ በዛፍ ምክንያት ወደ ሕይወት ተሻገረ፡፡ ከፍጥረቱ ጋር ተቃርኖ እንደሌለው እናውቅ ዘንድ