+251-993-818276 akofeda@gmail.com Addis Ababa, Ethiopia

አርዮሳውያንን አልቀበልም በማለቱ በመንግስት ዛቻ የደረሰበት ቅዱስ አባት

ቅዱስ ባስሊዮስ በ329 ተወልዶ በ379 በ50 ዓመቱ ከዚህ ዐመት እንግልት በእረፍት ተለየ፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ በዐለማዊ ትምህርቱ ከቅዱሳን አባቶቹ ሁሉ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዝ ሲሆን በመንፈሳዊ ሕይወቱ እና እውቀቱም የመነኩሴ ሊቅ እና በትሩፋቱም ቅዱስ ባስልዮስ ዘዐምድ ተብሎ የሚጠራ ታላቅ መንፈሳዊ አባት ነበር፡፡

ከነበረው ታላቅ መንፈሳዊ ትምህርት ዝግጅት እና መንፈሳዊነት ባሻገር ቅዱስ ባስልዮስ እንደ ቅዱስ አትናቴዎስ በጣም ደፋር ነበር፡፡ በአንድ ወቅት በወቅቱ የነበረው አላዊ ንጉስ ቫለንስ አርዮሳውያንን ይቀበል ዘንድ ሊያስገድደው ነፍሰ ገዳይ የሆነውን ሞደስተስ የሚባለውን አገረ ገዢ ልኮ ንብረቱን እንደሚወርስበት፣ አልፎ ተርፎም በተለያዩ ማሰቃያ መንገዶች እንደሚያሰቃየው፣ ከከተማውም በግዞት እንደሚያባርረው በመግለጽ እንዲያስፈራራው አደረገ፡፡

ቅዱስ ባስልዮስም ከጥቂት መጻሕፍት እና እጀ ጠባብ ውጭ የሚወረስ ንብረት እንደሌለው፣ ስለ መጋዝም መነኩሴ ስለሆነ የትኛውም የዓለም ክፍል እንደሚስማማው፣ ስለ መከራና ስቃይም እስትንፋሱ በመጀመሪያው ዱላ ቀጥ ስለምትል ቶሎ ፈጣሪውን እንዲያገኝ ስለሚያደርገው በዚህም ትልቅ ውለታ እየዋለለት እንደሆነ ነገረው፡፡ ‹‹ሞት ለኔ›› አለ ቅዱስ ባስልዮስ ‹‹ሞት ለኔ፡ ለተፈጠርኩለት፣ ለምኖርለት እና ለምፋጠንለት እግዚአብሔር የምቀርብበት የደግነት ሥራ ነው፡፡››

አረመኔው ሞደስተስም ድፍረት በተሞላው በቅዱስ ባስልዮስ መልስ በመደመም፤ ‹‹ከአሁን ቀደም ማንም ሰው በእንደዚህ ዐይነት ድፍረት መልስ አልመለሰልኝም›› አለው፡፡

ቅዱስ ባስልዮስም ‹‹ምናልባት ከአሁን ቀደም ክርስቲያን የሆነ መነኩሴ (ጳጳስ) አልገጠመህም ይሆናል፡፡ እኛ እሳትን፣ አውሬዎችን፣ ሥጋን ለማሰቃያነት የሚያገለግሉ የጭካኔ መሳሪያዎችን እንደ አስፈሪ (ሆረር) ከመመልከት ይልቅ እንደ አስደሳች ነገር ነው የምናያቸው፡፡ መከራ አድርሱብን፣ አሰቃዩን፣ አስፈራሩን፣ ማድረግ የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ፣ ኃይላችሁን በሙሉ በምትፈልጉት መልኩ ተደሰቱበት፣ ይሁን እንጂ ለንጉስህ ጭምር አንድ ነገር አሳውቅልኝ፤ በምንም ዐይነት ጭካኔ ብታስፈራሩን የናንተን ሐሰት እንቀበልም፡፡››

ከዛ ወዲህ ንጉሱ ቅዱስ ባስልዮስን አልተቃወመም፡፡ እሱም አገረ ገዢውም በጽናቱ ተገረሙ፡፡ (ዛሬ አብይ በአቡነ ማትያስ እንደሚገረመው)

በሌላ ወቅት የጳንጦስ አገረ ገዢ ቅዱስ ባስልዮስን ለፍርድ በማቅረብ ‹‹ጉበትህን ቀድጄ እንዳላወጣው›› በማለት ሊያስፈራራው ሞከረ፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ‹‹እባክህ አድርገው፤ አሁን ባለበት ሰላሜን እየነሳኝ ነውና›› በማለት መለሰለት፡፡

ቅዱስ ባስልዮስ በሕይወት ዘመኑ ላማንም አጎብድዶ አያውቅም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የሮሙን ፓፓ ዳማስየስ በምስራቁ የሀገር ክፍል ውስጥ የተፈጠረውን አለምግባባት ይሸመግል እና ያስታርቅ ዘንድ ይጠይቀዋል፡፡ ፓፓውም የበላይነቱን በሚያሳይ መንፈስ አስተናገደው፡፡ እሱም ለጳጳሳት ጉዋደኞቹ በደብዳቤ ቁጥር 239 ላይ ‹‹የምዕራቡን ዜና ታውቁታላችሁ፤ የመኮፈስ ነገር አለባቸው፡፡ እርዳታ ሲጠየቁ ከመቼውም በላይ ይንቀባረራሉ…..እግዚአብሔር ዘንበል ካለልን ሌላ ምን እንፈልጋለን? የእግዚአብሔር ቁጣ ግን በላያችን ላይ ከሆነ ከምዕራባውያን ትዕቢት ምናገኘው ምን ዕርዳታ አለ?›› በማለት ፈጣሪ ዘንበል ካለልን ምንም ኃይል እንደማይችለን ተናግሯል፡፡

ዛሬም የቅዱስ ባስልዮስን መንፈስ በአባቶቻችን ያሳየን ኃያሉ አምለክ ክብርና ምስጋና ይድረሰው፡፡

ምንጭ፡ The Faith of Our Fathers
By Paulos Mar Gregorious

Please follow and like us:
error0
fb-share-icon20

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Post

አንደኛው ዓለም ዐቀፍ ጉባዔ /የኒቂያ ጉባኤ/ (ሲኖዶስ) በ 325 ዓ.ም (ክፍል አንድ)

መንስኤው አርዮስ የሚባል ካህን የምንፍቅና አስተምህሮ ነው፡፡ መንስኤው አርዮስ የሚባል ካህን የምንፍቅና አስተምህሮ ነው፡፡አርዮስ ፡- በ 260 ዓ.ም በሊቢያ ከግሪካዊ ክርስቲያን ቤተሰብ ተወለደ፡፡በእስክንድርያም በአንጾኪያም በከፍተኛ ደረጃ የመጽሐፍቶችን የስነ መለኮት ትምህርት

ሲዖልን መሸጋገሪያ

ሁሉን ከምትሰለቅጠው ሲዖል በመስቀሉ ሰውን ወደ ሕይወት ያወጣው የጥበበኛው አናጺ ልጅ እነሆ፡፡ በዛፍ ምክንያት ወደ ሲዖል የወረደው የሰው ልጅ በዛፍ ምክንያት ወደ ሕይወት ተሻገረ፡፡ ከፍጥረቱ ጋር ተቃርኖ እንደሌለው እናውቅ ዘንድ

ዘመነ ጾም

የብልጽግናን እና የጣፋጭ ምግብን ጣዕም አትልመድ ምግብህ ቀለል ያለ እና የተመጠነ ይሁን መጽሐፍ ‹‹በሆድህ ጥጋብ አትሳሳት›› ይላልና (ምሳ 24፡15) ቴዎድሮስ ባሕታዊ ዘመነ ጾም ዘመነ ጾም የሚባለው በኢየዓርግና በኢይወርድ የተወሰነ ሆኖ