መንስኤው አርዮስ የሚባል ካህን የምንፍቅና አስተምህሮ ነው፡፡
መንስኤው አርዮስ የሚባል ካህን የምንፍቅና አስተምህሮ ነው፡፡
አርዮስ ፡- በ 260 ዓ.ም በሊቢያ ከግሪካዊ ክርስቲያን ቤተሰብ ተወለደ፡፡
በእስክንድርያም በአንጾኪያም በከፍተኛ ደረጃ የመጽሐፍቶችን የስነ መለኮት ትምህርት ተምሯል፡፡
የአንጾኪያው መምህሩ ሉቅያኖስ (የአርጌንስ ደቀመዝሙር እና የአንጾኪያ ትምህርት ቤት መስራች) ነበር፡፡
የክህደት ትምህርቱ ለአንጾኪያዊያን አስተምህሮ የቀረበ ነው፡፡
የንግግር ችሎታ ያለው እና ሰውን ማሣመን የሚችል አንደበተ ርቱዕ ሲሆን፤ በዚህም በተፍጻሚተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ድቁናን ተሾመ ፡፡
ከመንፈሣዊ ትምህርት በተጨማሪ የግሪክ ፍልስፍናም በደምብ የተማረ ነው፡፡
ከሉቅያኖስ በተጨማሪ የተሳሳቱ የሥላሴ አስተምሮዎቹን ከእስክንድሪያው ሊቅ ከአርጌንስም እንደተጠቀመ ይጠቀሳል፡፡
የአርዮስ ትምህርት ፡-
አብ ብቻ ዘለዓለማዊ (ዘአልቦ ጥንት ወኢተፍፃሜት)
ወልድ ዘለዓለማዊ አይደለም፡፡ ያልነበረበት ጊዜ ነበር (ሀሎ አመ ኢሄሎ) ስለዚህ አብ ከዘመናት በፊት ‘አብ’ አይባልም ፤ አብ መባል የጀመረው ከወልድ መፈጠር በኋላ ነው፡፡ በመሆኑም ‘ወልድ ፍጡር ነው’
ለወልድ ጥበብ ፣ ቃል የሚባሉ የኃይላት ስሞች አሉት፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚጠቅሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ምሳ 8÷22 ፣ ዩሐ 14÷28 ‘‘አብ ከእኔ ይበልጣል’’ ፣ “ጥበብ ከፍጥረቱ ሁሉ አስቀድሞ እኔነረ ፈጠረኝ አለች ’’ የሚለውን ነው፡፡
ወልድ በባሕርይው ከአብ ጋር አንድ አይደለም ፤ ይሁን እንጂ ከሌሎች ፍጡራን ይበልጣል፡፡ ለዚህም “ወልድ’’ በጸጋ የአብ ልጅ ይባላል፤ የፀጋ አምላክ ይባላል፡፡ ስለዚህ ም እንደፍጡርነቱ የአብን ባሕርይ ማየትም ማወቅም አይችልም፡፡
መንፈስ ቅዱስ ለወልድ የመጀመሪያ ፍጥረቱ ነው፡፡
ምክር እና ተግሣጽ
ይህን የተሳሳተ ትምህርቱን የሰማው ቅዱስ ጴጥሮስ (ተፍጻሜተ ሰማዕት) ጠርቶ በመምከርና ስህተቱን እንዲያስተካክል ቢነግረውም እምቢ በማለት ትምህርቱን በስፋት መናገር ቀጠለ፡፡ በዚህም አውግዞ ከዲቁናው ሽሮታል፡፡ ይህን ሲያደርግ በራዕይ ጌታ አርዮስ ልብሱን ሲቀድ በማየቱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህን ራዕይ ያየው በድዮቅሊጥያኖስ ተይዞ ለመገደል በእስር ላይ እያለ ነበር፡፡
አርዮስ ይህን አውቆ (ቅዱስ ጴጥሮስ ሊገደል እንደሚችል) ከእስራቱ እንዲፈታው ሽማግሌ ቢልክበትም ከጌታ በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት ከውግዘቱ ሳይፈታው ቀርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለደቀመዛሙርቱ ለእለእስክንድሮስ እና ለአርኬላዎስ አርዮስን ከውግዘቱ እንዳይፈቱት አስጠንቅቋቸዋል፡፡
ከቅዱስ ጴጥሮስ በኋላ በእስክንድርያ መንበር ላይ ፓትሪያርክ ሆኖ የተሾመው አርኬላዎስ አርዮስ የተፀፀተ መስሎ ስለቀረበውና ጓደኞቹም በምልጃ ስለለመኑት የመምህሩን ማስጠንቀቂያ ትቶ ከውግዘቱ የፈታው ሲሆን ቅስናም ሾሞታል፡፡
ከአርኬላዎስ በኋላ ዘመኑን ሁሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲጋደል የኖረው ስመጥሩው እለእስክንድሮስ በእርሱ ቦታ በእስክንድርያ መንበር ላይ ፓትሪያርክ ሆኖ ተመርጧል፡፡
እርሱም የአርዮስን ትምህርት ተቃውሞ አወገዘው፡፡ እንደቀድሞው ብዙ አማላጅ ቢልክለትም ጌታ በራዕይ መመለሱን ሲያሳየኝ ብቻ ነው የምፈታው በማለት አሻፈረኝ ብሏል፡፡
አርዮስም ብዙ ሰው በቀላሉ ሊከተለው እና በትምህርቱ ሊማረክ በሚችል መልኩ ትምህርቱን በግጥም በዘፈን (በመዝሙር) በመነባንብ እያደረገ ማሰራጨት ችሎ ነበር፡፡ ይህም ሥራው “ታሊያ ወይም ማዕድ›› ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡