+251-993-818276 akofeda@gmail.com Addis Ababa, Ethiopia

ሠማያት ተከፈቱ

ውድ ወንድሞች፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በጽርሐ-ጽዮን በላይኛው ቤት ስለ ተሰራጨው መንፈስ ቅዱስ የበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለትን አስመልክቶ ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ እነዚህ ተካተዋል፡፡

‹‹ዛሬ ከሰማይ መና ወይም እሳት ሳይሆን የወረደው የመልካም ነገሮች ምንጭ የሆነ መንፈሳዊ ማዕበል ነው፡፡ ሠማያዊው ዝናብ የዘነመው፣ መሬት ፍሬ እንድታፈራ ሊያደርግ ሳይሆን የሰው ዘር የመልካምነቱን ፍሬ ያቀርብ ዘንድ ለማሳመን ነው፡፡ ከዚህ የዝናብ ጠብታ የተቀበሉ ወዲያው እራሳቸውን በመዘንጋት በድንገት ምድር በመላእክት ተሞላች፡፡ በሰማያውያን መላእክት ሳይሆን በግዙፍ አካላቸው የረቂቃን መላዕክትን ግብር በሚያንጸባርቁ መሬታዊያን መላእክት፡፡››

ዛሬ ከሁሉ በላይ የምትሆን፣ የመዳኛ ታቦት፤ ሐዋርያት የሰሯት ቅድስት ቤተክርስቲያን የተገለጸችበት ቀን ነው፡፡ ዛሬ የጥፋት መርዝ ተሰባብሮ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የዕርቅ ማሕተም የታተመበት ቀን ነው፡፡ ይህ የሆነው እግዚአብሔር የሰው ልጅ ጠላት ስለነበር ሳይሆን የሰው ልጅ በራሱ እና በእግዚአብሔር መካከል ግርግዳን ስላበጀ ነው፡፡

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በእውነተኛዋ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል በቤተክርስቲያን ውስጥ በእግዚአብሔር ርህራሄና እግዚአብሄርን በማወቅ ፍሬ የሰው ልጅ ልብ ይታረሳል ይለሰልሳል፡፡ ከዘሬ ጀምሮ ተስፋ መቁረጥ ወይም መንፈሳዊ ባርነት የለም፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እየመራ መንፈሳዊ ልጆች አድርጎ የጥበብ ሃብትን ያከፋፍለናል፡፡ እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ሁላችንም የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ዕቃዎች ነን፡፡

መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ እንዳለ የሚያሳዩ የቅዱሳን አበውን አስተምህሮ ተውሼ እነግራቸሁ ዘንድ ትፈቅዱልኝ ዘንድ እማጸናለሁ፡-

በመጀመሪያ ዮሐንስ ዘደማስቆ ይህንን ዕለት አስመልክቶ ባስተማረው መልዕክት ‹‹ከእግዚአብሔር የተላከ ፀጋ››  ብሎ ይጠራዋል፡፡ እነዚህ በዚሀ ፀጋ የተሞሉ፡- እነደ መብረቅ አንፀባረቁ፣ ወደ ሚያምር እና እንግዳ ወደ ሆነ ነገር ተለወጡ፡፡ ይህ ከእግዚአብሔር የተላከ ፀጋ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሆኖ በጰራቅሊጦስ ዕለት ወደ ምድር የወረደ ሕግ ነው፡፡ ከሐጢአት እና ከሞት ነጻ የሚያወጣን ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ሕግ››፡፡ የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሕብረት እንዲኖራቸው ለሚፈልጉ ሕይወትን የሚያድል መንፈስ፡፡ በመሆኑም የኃጢአት ባርያ የነበረ የእግዚአብሔር የፀጋ ልጅነት ወደ መሆን የሚለወጥበት ፀጋ መንፈስ ቅዱስ፡፡

በዐይን የምናየው እሳት ፣ ለስላሳ የሆነውን የሸክላ ጭቃ ወደ ጠንካራ ሸክላነት እንደሚቀይረው እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ አስተዋይ ነብሲ ሲያገኝ፣ ምንም እንኳን ከሸክላ ጭቃ የለሰለሰች ብትሆንም እንደ ብረት ያጠነክራታል፡፡ ምንም እንኳን አንድ ሰው በኃጢአት እርኩስት አስቀድሞ የነበረ ቢሆን ወዲያው እንደ ፀሐይ የሚያበራ ይሆናል፡፡

ሁለተኛ፡- ከእግዚአብሔር የተላከው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከቤተክርስቲያን ሕይወት ተለይቶ አያቅም፡፡ እሱ ‹‹በሁሉ ነገር ውስጥ የሚገኝ እና የትም ቦታ ያለ ነው፡፡ የመልካም ነገር ሁሉ መዝገብ እና ሕይወትን የሚሰጥ ነው፡፡›› ለዚህ ነው የቤተክርስቲያን ማሕሌታይ እንዲህ ያለው ‹‹መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ነገር ይሰጣል፣ ለነቢያት መጻኢውን ይገልጥላቸዋል፣ ክህነትን ፍጹም ያረጋል፣ ላልተማሩት ጥበብን ይገልጣል፣ አላዋቂ የሆኑ አሣ አጥማጆችን ጠቢባን እና የነገረ መለኮት ልሂቃን ያረጋል በቅድሰት ቤተክርስቲያን ፍጹም አደረጃጀትን ያበጃል፡፡ አጽናኙ ሆይ፣ በኃይልና በግርማህ ከአባትህና ከልጁ ጋር አንድ የሆንክ ስለዚህ ለአንተ ክብር ምሥጋና ይገባል››

እሱ እግዚአብሔርን ወደማወቅ ይመራናል

ዛሬም ወደፊትም ለነቢያት የሚመጣውን ይገልጽላቸዋል

ለካህናት ፀጋን ይሰጣቸዋል

አስደናቂ እና አስደማሚ የሆነ የመፈወስ ሥራን ይሰራል

ለድውያን ሕይወትን ይሰጣል

ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ እንዲህ እያለ ይተርካል፡- ‹‹እርሱ የግብር ሰብሳቢው ማቴዎስን በማመኑ ወንጌላዊ ካደረገው፣ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዐሣ አጥማጅን፣ የነገረ መለኮት ልሂቅ ካደረገ፣ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ተነሣሂ የሆነውን አሳዳጅ ለብዙ ከተሞች ሰባኪ እና ምርጥ ዕቃው ካደረገ››

በመሆኑም የጠላትን እና የኃጢአትን ኃይለ የሚያሰወግድ እና በእርግጠኝንትም ከቅድስት ቤተክርስቲያን የማይለይ ይህ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ፤  ያለ ገደብ ለክርስቲያን አማኞች የሚሰጥ፣ ወደ ንሠሃ የሚመራ፣ ከንጽሐ ሥጋ ወደ ንጽሐ ነፍስ፣ ከንጽሐ ነፍስ ወደ ንጽሐ ልቦና ከፍ በማድረግ የእግዚአብሔርን መንግስት የሚያስወርስ መንፈስ ነው፡፡

በ40 80 ቀን የልጅነትን ጥምቀት ስንጠመቅ ክርስቶስን እንደምንለብሰው፣ መንፈስ ቅዱስንም እንለብሳለን፡፡ አለባበሳችንም እንደ ልብስ ሳይሆን በእሳት እንደ ጋለ የብረጥ ጥሩር ነው፡፡ እናም አጽናኙ የእያንዳንዱን ልቦና ሲሞላ፤ ዐይናቸው ያበራል፣ ጆሮዋቸው ይቀደሳል፣ ማስተዋላቸው ጨምሮ በጥበብ ይሞላሉ፣ ልክ የቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ፊት እነድ መልአክ ፊት እንዳበራ ፊታቸው በደስታ ያበራል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል እያንዳንዱ ክብረ በዓል በሰቂለ ህሊና እንጂ በዘመን አይከበርም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት ላለው ለማንኛውም ሰው፤  ሁሌም ትንሣኤ ነው፤ ሁሌም ጥምቀት ነው፣ ሁሌም ጰራቅሊጦስ ነው… ምክንያቱም እነሱ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች ናቸውና፡፡ ለእነዚህ በዚህ መድር ጀምሮ በመንግስተ ሰማያት የሚቀጥል የዘላላም ሕይወት እንጂ ሞት የሚባል የለባቸውም፡፡

በመቀጠል እነዚህን ጥያቄዎች ልንጠይቅ ይገባናል፡- የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆን ለኔ አስፈላጊ ነው? ሕይወቴን የመምራትን ነገር ለመንፈስ ቅዱስ ሐላፊነት አሳልፌ መስጠት ይኖርብኛል? የዚህ አጽናኝ አገልጋይ ለመሆን ብቁ ነኝ?

ሁላችሁም በዚሀ ቀን መንፈስ ቅዱስን ትቀበሉ ዘንድ፣ ሕይወታችንን ይቀይር ዘንድ ለመንፈስ ቅዱስ ማደሪያነት የተገባን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ እና ባደረብን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ አማካይነትም እርስ በእርስ እንፋቀር ዘንድ እጸልያለሁ፡፡

በአባ ሴራፊም

Please follow and like us:
error0
fb-share-icon20

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Post

ኦርቶዶክሳዊ አባት ፍለጋ

‹‹ቤተክርስቲያን ያለ ጠባቂ ነበረች መልካም የሆነ ጠፍቶ ክፋት ግን በሁሉ ቦታ ነበር ፡ወቅቱ መብራት በሌለበት ጭለማ እንደመጓዝ ነበር፡፡ ክርስቶስ ተኝቶ የቁስጥንጥንያ ባሕር ለተወሰነ ጊዜ በአርዮሳውያን እጅ ነበር፡፡ በዚህ ያገኘሁት ምንም

ማነው እንደ መጻጉዕ ያልታመመ?

ጸሎት እንዴት ተወዳጅ ነገር ነው፡፡ ሥራውስ እንዴት ያማረ ነው፡፡ ጸሎት ከመልካም ሥራ ጋር ሲደረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ በይቅርታ መንፈስም ሲደረግ፤ ወደ ላይ ሲያርግ ሁሉ ይታወቃል፡፡ ከልብ የተደረገ ንጹህ ጸሎት

ሆሣዕና

በዲን. በረከት አዝመራ “እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ ዘንድ እንድትሆን እኔም በእነርሱ…።” (ዮሐ. 17፥26)***የሆሣዕና ባህል ለፋሲካ መሥዋዕት ወደ ኢየሩሳሌም የሚገቡ በጎች የአምሳልነታቸው ፍጻሜ የሆነው መድኃኒት ክርስቶስ “ኢየሩሳሌም የቀዳችለትን የመከራ ጽዋ ይጠጣ