በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
ምንጭ፡ The Fathers of the Church Patristic Series 91
ጌታችን በሞት ላይ ተረማመደ፡፡ ከሞት ባሻገር ላለ መንገድም መረማመጃን አዘጋጀ፡፡ በሞት መንገድ ሞትን ያለፈቃዱ ያስወግደው ዘንድ በፈቃዱ ለሞት የተገዛ እና ሞትን የታገሰ እሱ ነው፡፡ ጌታችን መስቀሉን ተሸክሞ ሞት እንደሚሻው ተጓዘለት፤ ይሁን እንጂ በመስቀል ላይ ሳለ ከሞት ፈቃድ ውጭ ሙታንን ከሲዖል ያወጣቸው ዘንድ ወደ ሙታን ተጣራ፡፡ ሞት ለመግደያነት በተገለገለበት መሳሪያ ፣ ሞት ላይ ድልን ተቀዳጀ፡፡ መለኮት በሥጋ ተሰውሮ ወደ ሞት በመቅረብ ሞትን ሞቶ ገደለው፡፡ ሞት የተፈጠረች ሕይወትን ገደለ፡፡ ከፍጥረት ባሻገር የሆነች ዘላለማዊ ሕይወት ግን ሞትን ገደለችው፡፡
መለኮት በሥጋ ተሰውሮ ወደ ሞት በመቅረብ ሞትን ሞቶ ገደለው፡፡ ሞት የተፈጠረች ሕይወትን ገደለ፡፡ ከፍጥረት ባሻገር የሆነች ዘላለማዊ ሕይወት ግን ሞትን ገደለችው፡፡
ሞትም ሆነ ሲዖል ሥጋ ያልለበሰን መዋጥ አይሆንላቸውምና፤ እራሱን ለነሱ (ለሲዖል እና ሞት) በሚያመች መልኩ ያቀርብ ዘንድ ወደ ድንግል መጣ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረበበት ወቅትም ጥፋቷን እና ፍልሰቷን ይናገር ዘንድ የሚቀመጥበት አህያ አመጡለት፡፡ ከደንግል በነሳው ሥጋ መቃብርን ሰብሮ ወደ ሲዖል በመውረድ በመቃብር ካዝና ውስጥ የነበረቱን ነፍሳት አጋዘ፡፡ በዛም የሕያዋን ሁሉ እናት ወደ ሆነችው ወደ ሔዋን መጣ፡፡ እሷ ፍሬዋን ትቀምስ ዘንድ በእራሷ እጅ ሞት አጥሯን የሰበረባት የወይን ግንድ ነች፡፡ የሕያዋን ሁሉ እናት የሆነችው ሔዋን ለሕያዋን ሁሉ ሞት ምክንያት ሆነች፡፡ ከአሮጌዋ ወይን ከሔዋን የተገኘቸው አዲሲቱ እንቡጥ ማርያም ግን በውስጧ ሕይወት ተገኘ፡፡ ሞት እንደለመደው፤ በእርግጠኝነት፤ መዋቲ ነው ብሎ ያሰበውን ፍሬ ሊውጥ ሲመጣ፤ የሞት መግደያ፤ ሕይወት፤ ከውስጥ ሆኖ ይጠብቀው ነበር፡፡ ሞትም፤ ያለምንም ማመንታ ሕይወትን ቢውጠው፤ የዋጠው አስመለሰው፡፡ ከሕይወትም ጋር አብሮም ብዙዎችን ተፋቸው፡፡
የሞትም ጨጓራ መራር የሆነውን የሕይወት መድኃኒት በመዋጡ ታወከ፤ ይህቺን መድኃኒት ለማስመለስ ሲፈልግም በደስታ የዋጣቸውን እና በካዝናው ያከማቻቸውን ሕያዋን ሁሉ አብሮ ለማስመለስ ተገደደ፡፡
ስለዚህ የሕይወት መድኃኒት፣ ከሰማይ በርሮ ወርዶ፣ በምድር መዋቲ የሆነውን ፍሬ፣ ሥጋን ተዋሐደ፡፡ ሞት እንደልማዱ ሊመገብ ወደ ፍሬው ቢመጣ፤ በፋንታው በሕይወት ተዋጠ፡፡ ይህች ፍሬ ሊበሏት የሚሹት ረሃብተኞች የሚመገቧት ምግብ ነች፡፡ ስለዚህ ሞት ተስገብግቦ የዋጣቸውን ብዙ ነፍሳት ፤ ተርቦ በዋጣት በአንዲት ፍሬ ምክንያት ተፋቸው፡፡ ብዙዎችን ተስገብግቦ የዋጠው ሞት ይህቺን አንዲት ፍሬም እስኪውጥ ረሃብ ጠናበት፡፡ ብዙዎችን በመዋጥ ልማድ ያደረገው ሆዳምነቱ፣ ይህቺን አንዲት ፍሬ እስኪውጥ ድረስም አስቸኮለው፡፡ በእርግጥም ይህቺን ፍሬ በጥድፊያ ዋጣት፤ ይሁን እንጂ ይህቺ የዋጣት ፍሬ እራሷን ጨምሮ ብዙዎችን እንዲያስታውክ አደረገችው፡፡ ይህቺ አንዲት ፍሬ፤ በመስቀል ላይ እየሞተች ባለበት ሰዓት፤ ብዙ ሙታን ከሲዖል ድምጽዋን በመስማት እየወጡ ነበር፡፡
ይህቺ ፍሬ ከሞት ያመለጠች ፍሬ ናት፡፡ ይህቺ ፍሬ ሞትን እራሱን የዋጠች ፍሬ ናት፡፡ ይህቺ ፍሬ ከተጣለችበት ሲዖል ብዙ ነፍሳትን ይዛ የወጣች ፍሬ ናት፡፡ ሲዖል የዋጠቻቸውን ሁሉ የምታከማችበት ካዝና ነበራት፡፡ ነገር ግን በአንድ ምክንያት፣ መዋጥ የማይገባትን በመዋጧ፤ እስከ አሁን ውጣ ያከማቸቻቸውን ሁሉ መመለስ ግድ ሆነባት፡፡ ሰው ጨጓራው ሲታወክ የተስማማውም ያልተስማማውም ከሆዱ ይወጣል፡፡ የሞትም ጨጓራ መራር የሆነውን የሕይወት መድኃኒት በመዋጡ ታወከ፤ ይህቺን መድኃኒት ለማስመለስ ሲፈልግም በደስታ የዋጣቸውን እና በካዝናው ያከማቻቸውን ሕያዋን ሁሉ አብሮ ለማስመለስ ተገደደ፡፡
ይቆየን