
በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
ምንጭ፡ The Fathers of the Church Patristic Series 91
ለሟች ሁሉ የሕይወት ምንጭ ይሆን ዘንድ የሟች አዳምን ሥጋ ለለበስክ ለአንተ ክብር ይገባሃል፡፡ አንተ፤ ብዙ ፍሬ አፍርታ እንድትበቅል፣ ወደ ጥልቅ ጉድጓድ እንደ ዘሯት የስንዴ ቅንጣት፤ ገዳዮችህ የዘሩሕ ብቻህን ሕያው የሆንክ የሕይወት ዘር ነህ፡፡
ኑ፡፡ ፍቅራችንን በአንድነት ታላቅ ማዕጠንት አድርገን እናቅርብ፡፡ ኑ፡፡ ደሙን ስለኛ ላፈሰሰው እና መስቀሉን ለመለኮቱ ማዕጠንት አድርጎ ላቀረበው ለአንዱ፣ ጸሎታችንን እና መዝሙራችንን እንደ ዕጣን እንሰዋለት፡፡
በላይ በከፍታ የሚኖረው እራሱን በምድር ወዳሉት ዝቅ አድርጎ ሃብቱን አከፋፈላቸው፡፡ ቸግሯቸው ሰውነቱን የሻቱትም፣ ቀርበው ከመለኮቱ ስጦታን ተቀበሉ፡፡ የተዋሃደውን ሥጋም የሃብቱ ገንዘብ ያዥ አደረገው፡፡ ጌታ ሆይ ከካዝናህ ገንዘብህን አውጣና ለተቸገሩት የቤተሰብህ ወገኖች አከፋፍላቸው፡፡
የእርሱ የሆነውን የእኛ በሆነው አብዝተን እንቀበል ዘንድ፣ የእኛ የሆነውን ለወሰደ ለእሱ ክብር ይገባዋል፡፡ አስቀድሞ ሰው ሞትን የተቀበለው በመካከል ላይ ከቆመው እንደሆነ ሁሉ፤ አሁንም ሕይወትን ያገኘው በመካከል ሆኖ ከሚረዳን ነው፡፡ የሚወዱህ ሁሉ ፍቅርህን ይቀበሉበት ዘንድ መገልገያ የሚሆንህን የራስህን ሰውነት ፈጠርክ፡፡ የሚታይ ሥጋን በመልበስህ የገዳዮችህን እና የቀባሪዎችህን የተደበቀ ዓላማ ገለጥክበት፡፡ ገዳዮችህ የገደሉህ አንተም እነርሱን የገደልከው በሰውነትህ ምክንያት ነው፡፡ በሰውነትህ ምክንያት የቀበሩህን በሰውነትህ ምክንያት አስነሳሃቸው፡፡ ፍቅራቸው ቢቀብርህም እምነታቸው አብሮህ ተነሳ፡፡ የሚሹት፣ ሰውነቱን በመዳበስ መለኮትነቱን ያውቁ ዘንድ ያ የማይደረስበት ኃይል ዝቅ ብሎ ሰውነትን ለበሰ፡፡ በሰውነቱ ባለች ጣት አማካይነት ወደ ዲዳው ጆሮ በመጠጋት ምላሱን ነካለት፡፡ በሚነካ’ው ጣቱ ምክንያት የማይነካ’ውን መለኮቱን ዲዳው በመንካቱ ምላሱ ተፍታታ የማይደረስበት ጥልቁ የጆሮው ታምቡርም ተከፈተለት፡፡ ሥጋን አዋቅሮ ሰውነትን የሰራው፣ ወደ እርሱ በመቅረብ በለስላሳ ድምጾቹ ሕመም አልባ በሆነ መልኩ ጆሮውን ከፈተለት፡፡ መናገር የማይችልና የተዘጋ አንደበትም፣ ከደካማ አንደበቱ ቃላት እንዲወለዱለት ላደረገው ለእርሱ ምስጋናን አቀረበ፡፡ አዳምን ሳይማር እንዲናገር ያደረገው እርሱ፤ ምላሱ የሚተሳሰርበትን ዲዳውን ያለ ችግር እንዲናገር አደረገው፡፡
ይቆየን!!