ሁሉን ከምትሰለቅጠው ሲዖል በመስቀሉ ሰውን ወደ ሕይወት ያወጣው የጥበበኛው አናጺ ልጅ እነሆ፡፡ በዛፍ ምክንያት ወደ ሲዖል የወረደው የሰው ልጅ በዛፍ ምክንያት ወደ ሕይወት ተሻገረ፡፡ ከፍጥረቱ ጋር ተቃርኖ እንደሌለው እናውቅ ዘንድ መራራነትን ከቀመስንባት ዛፍ ጥፍጥናንም ቀመስን፡፡ ነፍሳት ከሲዖል ወጥተው ወደ ሕይወት ይሻገሩ ዘንድ መስቀልህን በሞት ላይ ለሰቀልክልን ለአንተ ክብር ምስጋና ይድረስህ፡፡
አማንያንም፣ ኢኣማንያንም የተሰናከሉበትን የጣዖት አምልኮ በመስቀልክ ላስወገድክ ላንተ ክብር ይገባሃል፡፡ ሕይወት መስሏቸው ወደ አዘቅት የወረዱትን፣ ወደ እውነተኛው ሕይወት ለመለስክ፣ የሕይወት መድሐኒት ለሆንከው ለአንተ ምስጋና ይገባሃል፡፡ ጠፍተው የተገኙቱ ያመሰግኑሃል፤ የጠፉትን በማግኘትህም፣ ያልጠፉት እና ሁሌም የሚኖሩቱን መላዕክት ደስ አሰኘሃቸው፡፡ በሰላምህ ፣ በመካከል የነበረውን ጠላትነት አስወግደህላቸዋልና ያልተገዘሩቱ ያመሰግኑሃል፡፡ ውጭያዊ ምልክት የሆነውን እና ያንተ የሆኑት ያንተ ለመሆናቸው የሚለዩበትን ግዝረት በሥጋህ ተቀብልክ፡፡ የተገዘሩቱ በመገዘራቸው ብቻ ያንተ እንዳልሆኑ ይታወቅ ዘንድ የልብ መገዘርን ምልክት አድርገህ ሰጠኸን፡፡ ያንተ ወደ ሆኑት መጣህ፣ እነርሱ ግን አልተቀበሉህም (ዮሐ 1፡11)፣ ያአንተ ያልሆኑቱ ግን ከልጆች የተረፈውን ፍርፋሪ ታበላቸው ዘንድ በኋላህ ያለቅሳሉ፡፡
በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
ምንጭ፡ The Fathers of the Church Patristic Series 91